ሀዲያ ሆሳዕናዎች አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።
ሀዲያ ሆሳዕናዎች ስሑል ሽረን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ አዳማ ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡና ላይ ድል ካደረገው ቋሚ ዳግም ተፈራ እና ኤልያስ ለገሰን አስወጥተው በናትናኤል ተፈራ እና ሙሴ ኪሮስ ተክተው ገብተዋል።
በሁሉም ረገድ ተመጣጣኝ ፉክክር በተደረገበት እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች ባስመለከተን የመጀመርያው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለመጫወት ሲሞክሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ፈጥረዋል።
አሜ መሐመድ አሻግሯት ሬድዋን ሸሪፍ በግንባሩ ባደረጋት ሙከራ ማጥቃታቸው የጀመሩት አዳማዎች በአሜ መሐመድ አማካኝነት ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል፤ ተጫዋቹ በቀኝ መስመር ያገኛትን ኳስ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ በጥሩ ብቃት ያወጣት እንዲሁም አድናን ረሻድ አሻግሯት በጥሩ መንገድ ተቆጣጥሮ ከሳጥን ውጭ መቷት የግቡን አግዳሚ በመለሳት ኳስ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር።
በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር የሞከሩት ነብሮቹም ሰመረ ሀፍታይ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኢዮብ ዓለማየሁ አሻግሯት ግብ ጠባቂ አልፋ የመጣችውን ኳስ ተንሸራቶ ወደ ግብነት ሳይቀይራት በቀረችው ወርቃማ ዕድል ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።
በአንጻራዊነት ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ግብ ያስተናገደው ገና በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ነበር። 47ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ በአዳማ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት የተገኘችውን ኳስ ገፍቶ በመግባት ለኢዮብ ዓለማየሁ አቀብሎት አጥቂው ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሩ ነብሮቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ አዳማዎች ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም አሜ መሐመድ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ ካወጣት ኳስ ውጭ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ሰመረ ሀፍታይ ከቀኝ መስመር አሻግሯት በሳጥኑ ውስጥ ነፃ የነበረው ተመስገን ብርሃኑ ሳያገኛት በቀረችው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበሩት ነብሮቹ ግን በ82ኛው ደቂቃ በበረከት ወልደዮሐንስ ግብ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ተከላካዩ ብሩክ ማርቆስ ከቆመ ኳስ ያሻገራትን በግንባሩ በመግጨት ነበር ያስቆጠረው።
አዳማዎች ከግቧ መቆጠር እስከ ጨዋታው ማብቂያ ድረስ ጫና በመፍጠር ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም በግብ ጠባቂው እና በተከላካዮች ጥረት ከሽፈዋል፤ አሸናፊ ኤልያስ በሁለት አጋጣሚዎች ከቆመ ኳስ አሻምቷቸው አሜ መሐመድ እና አብዲ ዋበላ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ቡድኑ ከፈጠራቸው የግብ ዕድሎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ድሉን ተከትሎ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን ያስመዘገቡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ16 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 3ኛ ብቅ ብለዋል።