መረጃዎች | 41ኛ የጨዋታ ቀን

የ11ኛ ሳምንት መክፈቻ የሆኑ ሁለት መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ወደ መሪዎች ይበልጥ የተጠጉት ብርቱካናማዎቹ
አጀማመራቸው ካላማረላቸው ሀምራዊ ለባሾቹ የሚያደርጉት ጨዋታ የ11ኛው ሳምንት ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ደረጃቸውን ያሻሻሉት ብርቱካናማዎቹ በአስራ አምስት ነጥቦች 4ኛ ላይ ተቀምጠዋል። ከመሪው በአምስት ነጥቦች ርቀት ያለው ቡድኑ ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት የነገውን ድል አጥብቆ ይፈልገዋል።

በመጨረሻው ጨዋታ በሁሉም ረገድ የተሻሻለ ብቃት ያሳዩት እና በጥሩ መንፈስ ጨዋታቸውን የከወኑት ድሬዳዋ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት የተስተዋሉባቸውን የአፈፃፀም ክፍተቶች በመቅረፍ በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድኖች ተርታ ተመድበዋል። 19 ግቦች ካስቆጠረው መቻል ቀጥሎ ብዙ ግቦች ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በተከናወኑ አራት መርሐግብሮች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር አልቻለም፤ በመጨረሻው መርሐግብር ግን ሦስት ግቦች ከማስቆጠሩም በተጨማሪ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠሩ የመሻሻሉ ማሳያ ነው። የኳስ መቆጣጠር ብቃቱ ከጨዋታ ጨዋታ ጉልህ መሻሻሎች ያሳየው የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ቡድን በነገው ጨዋታም ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ሰጥቶ ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ ከተጋጣሚው አቀራረብ አኳያ ሲታይ ግን ቀላል ፈተና እንደማይገጥመው እሙን ነው።

ከሰባት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦች በመሰብሰብ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ያሉት አጀማመራቸው ያላማረላቸው የዓምና ቻምፒየኖቹ ንግድ ባንኮች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በሁሉም ረገድ የተዳከመ እንቅስቃሴ ባሳዩበት የመጨረሻው መርሐግብር በባህርዳር ከተማ ሦስት ለባዶ የተረቱት ሀምራዊ ለባሾቹ ከሌላው ጊዜ በተለየ ደካማ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው የቡድኑ ዋነኛ ክፍተት ሆኖ አልፏል። የተጋጣሚን የመስመር እንዲሁም የፈጣን ሽግግሮች ለመግታት ሲቸገር የተስተዋለው ቡድኑ በጨዋታው ሦስት ግቦች ከማስተናገዱም በላይ ይበልጥ ተጋላጭ ሆኖ በርከት ያሉ ሙከራዎችን አስተናግዷል። ከዚህ ቀደም ቡድኑ አመርቂ እንቅስቃሴ ባላደረገባቸው ጨዋታዎችም ጭምር ጨዋታውን በተሻለ መንገድ መቆጣጠር መቻሉ የተጋጣሚ ጥቃቶች ሲመክት የነበረው ቡድኑ የአማካይ ክፍሉ መዳከም እና ጨዋታዎችን የመቆጣጠር አቅሙ መውረዱ የተከላካይ ክፍሉ ይበልጥ እንዲጋለጥ በር ከፋች ሆኗል።

ከመጨረሻው ጨዋታ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ በመከላከል አደረጃጀታቸው ደስተኛ እንዳልሆኑ የገለፁት አሰልጣኝ በጸሎት ልዑድሰገድ የተጠቀሰውን የቡድኑ ችግር ማስተካከል ቀዳሚ ሥራቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማም በተመሳሳይ በሽግግሮች እና በመስመር አጨዋወት የተካነ ቡድን እንደመሆኑ ችግሩ አንገብጋቢ መፍትሔ እንዲበጅለት ያስገድዳል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል መሐመድኑር ናስር በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም ፤ የመስዑድ መሐመድ ፣ ቻርለስ ሙሴጌ እና ጀሚል ያዕቆብ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ሱለይማን ሀሚድ በጉዳት መድረሱ አጠራጣሪ ሲሆን ፉዓድ ፈረጃ ግን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው አምስት
አምስት ጊዜ ሲሸናነፉ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 28 ጎሎች በተቆጠሩበት የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ አንድ ጊዜ ብቻ ግብ ሳይቆጠር የተጠናቀቀ ሲሆን ባንክ 15፣ ድሬ 13 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

ድል የናፈቃቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ለአሸናፊው የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝ እንደመሆኑ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።

ለተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ በማሳካት በድምሩ ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበው በወራጅ ቀጠናው ይገኛሉ።

ቡድኑ ከተከታታት ሦስት ሽንፈቶች አገግሞ ሁለት የአቻ ውጤቶች ከማስመዝገቡም በተጨማሪ ነጥብ በተጋራባቸው ጨዋታዎች በብዙ መንገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየት ቢችልም እንቅስቃሴውን ወደ ነጥብ መመንዘር አልቻለም። ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ደካማ የግብ ዕድሎችን የመጠቀም ብቃቱ ነው። በተለይም ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ በርከት ያሉ የጨዋታውን መልክ የሚቀይሩ ወርቃማ ዕድሎች ያባከኑት ኃይቆቹ ጉልህ የአፈፃፀም ድክመታቸውን ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።

በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ በውስን ተጫዋቾች ጫንቃ የተጣለውን የግብ ማስቆጠር ኃላፊነት ለሌሎች ተጫዋቾች ማጋራትም ይጠበቅበታል።

በአስር ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባ ምንጭ ከተማዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ደረጃቸውን ለማሻሻል እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

አዞዎቹ ሁለት ተከታታት ሽንፈቶች ካስተናገዱ በኋላ በሰንጠረዡ አራት ደረጃዎች እንዲያሽቆለቁሉ ሆኗል። ቡድኑ ከሽንፈቱም ባሻገር እስከ ቅርብ ሳምንታት በጥንካሬያቸው ዘልቀው የነበሩ ጥሩ ጎኖቹን አጥቷል። በተለይም በአራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ በቡድኑ ውጤት ትልቅ ድርሻ የነበረው እና በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐግብሮች አምስት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀቱ መሻሻሎች ይፈልጋል።

ግቦችን ማስቆጠር ባይችልም በቂ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት ሁኔታም ጭምር አስፈሪነቱ ያልቀነሰው በአሕመድ ሑሴን እና በ በፍቅር ግዛው የሚመራው የማጥቃት ጥምረት ቡድኑ ግምት እንዲሰጠው የሚያደርግ ጠንካራ ጎን ነው።

በሀዋሳ ከተማ በኩል እንየው ካሳሁን ከቅጣት በመመለሱ ሙሉ የቡድን አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በአርባምንጭ ከተማ በኩል አበበ ጥላሁን ለረጅም ግዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ሲታወቅ ቻርለስ ሪባኑ ለነገው ጨዋታ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። አሕመድ ሁሴን ከመጠነኛ ጉዳት ተመልሷል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 18 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ ስምንቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ ስድስት ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ አራት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ ግቦች 19ኙ የሀዋሳ 15ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።