ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ሊጠጋበት የሚችለውን ዕድል አምክኗል

በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት ቀዳሚ መርሃግብር እምብዛም ሳቢ ያልነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማዎች ሲዳማ ቡናን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገዱትን ኢስማኤል አብዱል ጋኒዩ እና መሀመድ ኑር ናስር በድልአዲስ ገብሬ እና ሙኸዲን ሙሳ ተክተው ሲገቡ በአንፃሩ ደካማ አጀማመር እያደረጉ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በባህር ዳር ከተማ ከተረታው ስብስብ ባደረጓቸው አራት ለውጦች ካሌብ አማንኩዋ ፣ ተመስገን ተስፋዬ ፣ ሳይመን ፒተር እና አዲስ ግደይን አስወጥተው በምትካቸው እንዳለ ዮሀንስ ፣ ተስፋዬ ታምራት ፣ አብዱልከሪም መሀመድ እና ዳዊት ዮሀንስን በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።
ሁለት ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሰጡ ቡድኖችን ባገናኘው ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች በመፈራረቅ ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም ሁለቱም ቡድኖች በመጨረሻቸው ሲሶ ላይ የነበራቸው አፈፃፀም ደካማ መሆኑ በአጋማሹ በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ዕድሎችን እንዳንመለከት አድርጎናል።

በአጋማሹ በአንፃራዊነት ኤፍሬም ታምራት በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል የተሻለ ጥቃት ለመሰንዘር የሞከሩት ንግድ ባንኮች በ9ኛው እና 23ኛው ደቂቃ ከኤፍሬም መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች የፈጠሯቸውን ሁለት ዕድሎች ኪቲካ ጅማ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።

በአንፃሩ በድሬዎች በኩል በ20ኛው ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ጀሚል ያዕቆብ ወደ ሳጥን ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ ሙኸዲን ሙሳ እንዳይጠቀምበት ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ለጥቂት ግብ ከመሆን የዳነችው አጋጣሚ እንዲሁም በ44ኛው ደቂቃ ላይ አቤል አሰበ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ያደረገውን ሙከራ ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እንደመጀመሪያው ሁሉ ሁለቱም ቡድኖች ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩበት ነበር ፤ በአጋማሹ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር በሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች በኩል የፊት መስመራቸውን ለማስተካከል ግለሰባዊ ለውጦች ቢደረጉም ይህ ነው የሚባል ለውጥ መመልከት ሳንችል ቀርተናል።
ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች በ16 ነጥቦች ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ የአምና ሻምፒዮኖቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ9 ነጥቦች ለጊዜውም ቢሆን ወደ አስራ አምስተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።