ሪፖርት| የበረከት ሳሙኤል ስህተት አርባምንጭን ባለ ድል አድርጋለች

አዞዎቹ ተቀይሮ በገባው አሸናፊ ተገኝ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ሐይቆቹን 1ለ0 በመርታት ሙሉ ሦስት ነጥብን አሳክተዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከመቐለው የአቻ ውጤት የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ማይክል ኡቱሉን በዳዊት ታደሠ ፣ ወንድማገኝ ሐይሉን በአቤኔዘር ዮሐንስ ሲተኩ አርባምንጮች በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ውስጥ ስቴፈን ባዱአኖርኬ ፣ መሪሁን መስቀሌ እና አህመድ ሁሴን አሳርፈው ብሩክ ባይሳ ፣ አንዱአለም አስናቀ እና አህዋብ ብሪያንን በቋሚ አሰላለፍ በማካተት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሁለቱን ቡድኖች ያገናኘው የምሽቱ መርሃግብር ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ የነበረው ቢሆንም ከጎል ሙከራዎች አኳያ ግን ድክመት የነበረበት ነበር።

በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች መጠነኛ ብልጫን አዞዎቹ ወስደው ቢታዩም በይበልጥ ወደ መስመር ቀስ በቀስ ማድላት የጀመሩት ሐይቆቹ ግን በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ብልጫውን ወስደዋል።

17ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዘር ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ባደረገው ሙከራ ጥቃት የሰነዘሩት ሀዋሳዎች በድግግሞሽ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ይገኙ እንጂ የአርባምንጭን አጥር ማስከፈቱ ከብዷቸው ተስተዋሏል።

ሀዋሳዎች ከሚሰሩት የቅብብል ስህተት አልያም ደግሞ ፈጣን መልሶ ማጥቃትን የሚጠቀሙት አርባምንጭ ከተማዎች 31ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ታረቀኝ በቅብብል ወቅት የተሳሳተውን ኳስ ሙሉጌታ ካሳሁን አግኝቶ ቢመታውም ሰዒድ ሀብታሙ ሳይቸገር ኳሷን ተቆጣጥሯታል።

ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ይሁን እንዳሻው በተመሳሳይ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ ያደረጋት ሙከራን የግብ ዘቡ ሰዒድ በንቃት ኳሷን ወደ ውጪ አውጥቷታል።

አጋማሹ ሊገባደድ በቀሩት አምስት ደቂቃዎች ሀዋሳዎች መሪ ሆነው ሊወጡ የሚችሉበትን ዕድል ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ፤ ዓሊ ሱሌይማን ከፋሪስ ዓለዊ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የመከነበት ኳስ በድጋሚ ያገኘው ቢኒያም በላይ አጋጣሚዋን ወደ ውጪ ሰዷታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ከመጀመሪያው በንፅፅር መጠነኛ መቀዛቀዞች የነበሩበት ነበር ፤ የሚቆራረጡ እንቅስቃሴዎች በይበልጥ ያስመለከተን አጋማሹ ሀዋሳዎች የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ በ56ኛው የአጥቂ ክፍላቸውን ካደሱ በኋላ በጨዋታው ብልጫውን ቢይዙም የመጨረሻው ሜዳ ደርሰው የግብ አጋጣሚን መፍጠሩ በእጅጉ ከብዷቸው ተስተውሏል።

ጥንቃቄን መርጠው የሚያገኟቸውን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት መጫወትን የመረጡት አርባምንጮች በብዙ ረገድ በተጋጣሚያቸው ብልጫ ቢወሰድባቸው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግን የሰሉ ጥቃቶችን ሰንዝረው ተስተውሏል።

ብልጫ የነበራቸው ሐይቆቹ ይባስ ብሎ 87ኛው ደቂቃ አርባምንጮች በላይ ገዛኸኝ ያለቀላት አጋጣሚን ፈጥሮ ካልተጠቀማት ከሁለት ደቂቃ መልስ በረጅሙ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል የተላከን ኳስ ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ወደ ኋላ ለግብ ጠባቂው ሰዒድ ለመስጠት ያቀበለው ኳስ ማጠሩን ተከትሎ ኳሷን ያገኘው ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ተገኝ የግብ ዘቡን ጭምር አልፎ አዞዎቹን መሪ አድርጓል።


ጎል ካስተናገዱ በኋላ በዓሊ ሱለይማን አማካኝነት ሀዋሳዎች አቻ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚን ቢያገኙም ሳይጠቀሙ መቅረታቸውን ተከትሎ በጨዋታው 1-0 ተሸንፈው ሊወጡ ግድ ብሏቸዋል።