11ኛ ሳምንት ላይ የደረሰው ሊጉ ነገ በሚደረጉ ሁለት መርሃግብሮች ሲቀጥል ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ባህርዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ሆነው የሚገናኙት የጣና ሞገዶቹ እና ፈረሰኞቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው በአምስት መርሃግብሮች ሳይሸነፉ የዘለቁት ባህርዳር ከተማዎች የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሸነፍ ኮስታራ ተፎካካሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
የጣና ሞገዶቹ በተከታታይ ካስመዘገቧቸው ውጤቶች በተጨማሪ በአስር ጨዋታዎች አራት ግቦች ብቻ ያስተናገዱ መሆናቸው ስለመከላከል አደረጃጀቱ ሁሉንም ነገር የሚጠቁም ነጥብ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም እንደ ቡድኑ ውጤት ሁሉ የወጥነት ችግር የነበረበት የፊት መስመር ጥምረቱ ውጤታማ መሆን ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት ክፍሉ በርከት ባሉ ተጫዋቾች ተዋፅኦ የተገነባ መሆኑ ጥንካሬ አላብሶታል።
ስምንት ጨዋታዎች አከናውነው አስራ አንድ ነጥቦች የሰበሰቡት ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ የጣና ሞገዶቹን ይገጥማሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጨረሻው መርሃግብር ጨምሮ በቅርብ ሳምንታት በተካሄዱ ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ ደረጃ መሻሻል አሳይተዋል። ምንም እንኳን ሽንፈት ባስተናገዱበት የመቻሉ ጨዋታ ለሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ከቆየ በኋላ ሦስት ግቦችን አስተናግዶ ለሽንፈት ቢዳረግም ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር በጨዋታው ያሳየው እንቅስቃሴ ግን ተስፋ ሰጪ ነበር።
ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየቱ ባይካድም በማጥቃቱ ረገድ ግን ውጤታማነቱ ቀንሶ ቆይቷል፤ ከሽንፈቱ በፊት በተካሄዱ ሦስት መርሃግብሮች አንድ ግን ብቻ ማስቆጠሩም የዚ ማሳያ ነው። በመቻሉ ጨዋታ ግን ምንም እንኳ ሽንፈት ብያስተናግድም በአምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደው ጠንካራው የኋላ ክፍል ላይ ሦስት ግቦች ማስቆጠሩ ለጣና ሞገዳቹ ተከላካዮች የሚያስተላልፈው መልዕክት ስለመኖሩ መናገር ይቻላል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል ፍሬዘር ካሳ ከቅጣት ይመለሳል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ክዋሜ ፍሪምፓንግ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታ ውጭ ሲሆን በረከት ወልዴ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ አስር ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ሦስት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሁለት ድሎችን አሳክተው አምስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ አስር ባህር ዳር ከተማ ዘጠኝ ግቦችን አስቆጥረዋል።
ሀድያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና
ተከታታይ አምስተኛ ድላቸውን በማስመዝገብ በሰንጠረቹ የላይኛው ክፍል ለመደላደል የሚያልሙት ሀድያ ሆሳዕናዎች እና ከናፈቃቸው ድል ለመታረቅ ወደ ሜዳ የሚገቡት
ሲዳማ ቡናዎች የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ነው።
አራት ተከታታይ ድል በማስመዝገብ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙት ነብሮቹ አስራ ስድስት ነጥቦች ሰብስበው በ4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣዋል።
ውጤትም ይሁን በሥነ ልቦና ደረጃ ጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች በብዙ ረገድ መለወጣቸው ካሳዩበት የአዳማ ከተማው ጨዋታ በኋላ መሪዎቹን እግር በእግር እንዲከተሉ የሚረዱዋቸው ወሳኝ ሦስት ነጥቦች ፍለጋ ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ። በቀጥተኛም እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችም ለመፍጠር የሚሞክረው ቡድኑ በመጨረሻው መርሃግብር በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥሯል። በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ካለው ታታሪነት በተጨማሪ በአጥቂ መስመር ላይ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ፍጥነት እና ታታሪነትም በነገው ጨዋታ ለሲዳማ ቡና አደጋ አምጪ እንደሚሆን ይታመናል።
በተከታታይ አራት መርሃግብሮች መረቡን ያላስደፈረው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀትም ለውጤቱ ማማር የአምበሳው ድርሻ የሚወስደው የቡድኑ ክፍል ነው።
ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች በአስራ ሦስት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።
ቡድኑ ተከታታይ ሽንፈት ከማስተናገዱም ባለፈ ከድል ጋር ከተራራቀ አራት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል፤ ከዚ በተጨማሪ ከውጤቱ ባለፈ በእንቅስቃሴ ረገድም መዳከሙ ታይቷል።
ተከታታይ አራት ድል በተቀዳጀባቸው መርሃግብሮች ስድስት ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ግን አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሯል። በመከላከሉ ረገድም ካየነው ድል ባደረገባቸው ቀዳሚ አራት መርሃግብሮች አንድ አስተናግዶ በተቀሩት ጨዋታዎች ደግሞ አምስት ግቦች አስተናግዷል።
ቁጥሮቹ እንደሚያሳዩት ቡድኑ በሁሉም ረገድ መሻሻሎች ይፈልጋል። በቅርቡ ውላቸውን ያራዘሙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከተጠቀሱት የማጥቃት እና የመከላከል ድክመቶች በተጨማሪ በቂ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለው የአማካይ ክፍል ላይም ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ወደ ልምምድ ከተመለሰው ጫላ ተሺታ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
በሲዳማ ቡና በኩል በመጨረሻው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ጊት ጋትኩት እና አምስት ቢጫ ካርዶች የተመለከተው ፍቅረኢየሱስ ተ\ብርሃን በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን አስር ጨዋታዎች አድርገዋል። ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 16 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና አራት ፣ 10 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ ሦስት ድሎችን አስመዝግበዋል።