አዳማ ከተማ በመጨረሻ ጭማሪ ደቂቃ ላይ በተቆጠረባቸው ጎል ከወላይታ ድቻ ጋር 2ለ2 ተለያይተዋል።
አራፊ ከመሆናቸው በፊት ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ተለያይቶ ከነበረው ስብስባቸው ወላይታ ድቻዎች የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ቢኒያም ገነቱ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ ሙሉቀን አዲሱ ፣ መሳይ ሠለሞን እና ካርሎስ ዳምጠው አርፈው አብነት ይስሀቅ ፣ ፍፁም ግርማ ፣ ብዙአየው ሰይፈ ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ብስራት በቀለ በቋሚ አሰላለፍ ተካተው ሲገቡ በሀድያ ሆሳዕና የተረቱት አዳማዎች ግን ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ቀርበዋል።
ቀዝቀዝ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ ባስመለከተን ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር ከማስናገድ ባለፈ ጥራት ባላቸው ሙከራዎች ያልታጀበ ነበር። በአጋማሹ ከነበረው ፉክክር ይልቅ 5ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው ሙሴ ኪሮስ እና የወላይታ ድቻው ናትናኤል ናሲሩ መሐል ሜዳ ላይ ዕርስ በዕርስ ተጋጭተው ጉዳት ያስተናገዱበት አጋጣሚ በጨዋታው ላይ በትኩረት ሊጠቀስ የምትችለዋ አጋጣሚ ሆናለች።
ዝግ ያለን እንቅስቃሴ እያስመለከተን የቀጠለው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች 12ኛው ደቂቃ ሲደርስ አዳማን መሪ ያደረገ ጎልን አስመልክቶናል። አሜ መሐመድ በቀኝ በኩል ከአድናን ጋር ተቀባብሎ ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ በግንባር ገጭቶ የልጅነት ቡድኑ መረብ ላይ ኳሷን አስቆጥሯታል። ከጎሏ በኋላ መጠነኛ የሽግግር ጨዋታን መከተል የጀመሩት አዳማ ከተማዎች 17ኛው ደቂቃ አድናን ከግራ መነሻ ሆና የደረሰችውን ኳስ በቀላሉ ካመከናት በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች ፈጣን በሆኑ እና ወደ መስመር በሚጣሉ ኳሶች በርካታ አጋጣሚዎችም የፈጠሩበት ነበር።
37ኛው ደቂቃ የግራው ሳጥን ጠርዝ ዘላለም አባተ አግኝቶ ወደ ጎል ሞክሮ የወጣችበት እንዲሁም ብዙአየው እና ብስራት የሚያስቆጩ ተከታታይ ዕድሎችን አግኝተው የናትናኤል ተፈራን የኋላውን በር ማግኘት ያልቻሉባቸው አጋጣሚዎች ተጠቃሾቹ ናቸው። 40ኛው ደቂቃ ላይ የጦና ንቦቹ ከመስመር ኬኔዲ አሻግሮ ተጨራርፋ ጎል ሆናለች በሚል የቡድኑ አባላት ተቃውሞ ቢያሰሙም የዕለቱ ዳኛ መስፍን ዳኜ ሳይቀበሉት አጋማሹ ተገባዷል።
ከዕረፍት ተመልሶ የቀጠለው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጣን የሆኑ እንቅስቃሴዎችን የተመለከትንበት ሲሆን አዳማዎች በተሻለ የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ብልጫውን የወሰዱበት ነበር። 63ኛው ደቂቃ በረጅሙ ወደ ተከላካይ የተጣለን ኳስ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያገኘው አድናን ተቆጣጥሮ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት አሻግሮ ነቢል ኑሪ ሁለተኛ ጎል በማድረግ የአዳማን የግብ መጠን ከፍ አድርጓል።
ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ በአጥቂ ክፍላቸው ላይ ዕድሳት ያደረጉት የጦና ንቦች በተደጋጋሚ የአዳማ ሳጥን ደርሰው ወደ ጨዋታ ለመመለስ በእጅጉ ጥረቶችን ማድረግ በጀመሩበት ሰዓት በቅብብል ወቅት አዳማዎች የሰሩትን ስህተት መሳይ ሠለሞን አግኝቶ ቢሞክረውም የግብ ዘቡ ናትናኤል ተፈራ ጥሩ ብቃት ኳሷ ጎል እንዳትሆን አስችሏል።
ጫና መፍጠራቸውን በይበልጥ አጠናክረው የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይረው የገቡት መሳይ እና ካርሎስ በፈጠሩት ጥምረት ግዙፉ አጥቂ ካርሎስ በመጨረሻም ኳስን ከመረብ አሳርፎ ጨዋታውን ወደ 2ለ1 ሲያሸጋግር 85ኛው ደቂቃ ላይም ራሱ ካርሎስ የሚያስቆጭ ዕድልን ፈጥሮ በግቡ ቋሚ ብረት የተመለሰችበት እና ናትናኤል ከርቀት አክርሮ መቶ በግብ ዘቡ ናትናኤል የከሸፈችዋ የወላይታ ድቻዎች አስቆጪወቹ ሙከራዎች ናቸው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ ፍፁማዊ ብልጫን ያሳዩት ድቻዎች 90+6 ላይ መሳይ ሠለሞን የአቻነት ጎል አስቆጥሮ በመጨረሻም ጨዋታው 2ለ2 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።