በ11ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን የምሽት መርሃግብር ወልዋሎ ዓ.ዩ ዳግም በተመለሱበት ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ነጥባቸውን ከ9 ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ከኢትዮጵያ ቡና ወስደዋል።
በ10ኛ የጨዋታ ሳሞንት አርባምንጭ ከተማን የረቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት የመጀመሪያ 11 ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ኮንኮኒ ሀፍዝን በአማኑኤል አድማሱ ብቻ ሲተኩ በአንፃሩ የመጀመሪያ ነጥባቸውን እያሰሱ የሚገኙት ወልዋሎዎች በመጨረሻው ጨዋታቸው በፋሲል ከተረታው ስብስብ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ናትናኤል ኪዳኔ ፣ ሚራጅ ሰፋ እና ዳዊት ገብሩን አስወጥተው በምትካቸው በረከት አማረ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና አላዛር ሽመልስን ተክተው አስገብተዋል።
የኢትዮጵያ ቡና መጠነኛ የበላይነት በተስተዋለበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ችለዋል ፤ በ2ኛው ደቂቃ ከስንታየሁ ዋለጩ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ከተከላካዩች ሾልኮ የወልዋሎ ሳጥን የደረሰው አንተነህ ተፈራ ከበረከት አማረ ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረ ተብሎ ሲባል ወደ ውጭ በሰደዳት ሙከራ የጀመረው የቡናዎቹ ጥቃት በ20ኛው ደቂቃም እንዲሁ ስንታየሁ ዋለጩ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ ዋሳዋ ጂኦፌሪ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።
በሂደት ብዙ መልኩ ብልጫ ወስደው መንቀሳቀስ የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደ ነበራቸው የጨዋታ ቁጥጥር በቂ የጠሩ ዕድሎችን ግን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በአንፃሩ ወልዋሎዎች በአጋማሹ ለሳጥናቸው ቀርበው ከመከላከል በዘለለ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ደርሰው አደጋ ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውሏል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ ጋር በአመዛኙ ተመሳሳይ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአውንታዊነት በአንፃሩ ወልዋሎዎች ደግሞ ከመጀመሪያው በተሻለ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት አጋማሽ የነበረ ቢሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎችን ግን ለመመልከት ያልታደልንበት አጋማሽ ነበር።
ግዙፉን አጥቂ ሲዲ ማታላ እና ዳዊት ሽፈራውን በማስገባት ማጥቃታቸውን ለማሻሻል ያሰቡት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ሲቀር ይበልጥ ጥንቃቄን ጨምረው መጫወት ምርጫቸው ያደረጉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ዕቅዳቸው ፍሬያማ ነበር።
ጨዋታው 0-0 መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዋሎ ዓ.ዩ ዳግም በተመለሱበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ነጥባቸው ከሳምንታት ጥበቃ በኋላ አሳክተዋል።