መረጃዎች | 43ኛ የጨዋታ ቀን

ተጠባቂው የመዲናይቱ አንጋፋ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ጨምሮ ስሑል ሽረ እና መቐለ 70 እንደርታ የሚያደርጓቸው የጨዋታ ሳምንቱ መገባደኛ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

መቻል ከ ኢትዮጵያ መድን

በሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረው መቻል ጥቂት ግቦች ካስተናገደው መድን ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ ተጠባቂ መርሀ-ግብር ነው።

ሊጉን በሀያ ነጥብ በመምራት ላይ የሚገኙት መቻሎች በመሪነቱ ለመደላደል የነገው ድል አጥብቀው ይፈልጉታል።

በሲዳማ ቡና ከገጠመው የመጀመርያው ሳምንት ሽንፈት ማግስት ጠንክሮ የታየው መቻል ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች በአልቀመስ ባይነቱ ቀጥሏል።
ማግኘት ከሚገባው ሀያ ሰባት ነጥቦች ሰባት ነጥቦች ብቻ ጥሎ ሀያውን ያሳካው ጦሩ በሁሉም የጨዋታ ሂደቶች የሚታዩት ቡድናዊ እንቅስቃሴዎች ውጤት እያስገኘለት እንደሆነ በጉልህ ተስተውሏል።
በተለይም በዘጠኝ ጨዋታዎች አስራ ዘጠኝ ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱ የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ነው። ቡድኑ በነገው ዕለት በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስተናገደና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን መግጠሙ ሲታሰብ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀዋል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም ባለፉት ጨዋታዎች የታየው የፊት መስመር ጥራት ነገም ከተደገመ የኢትዮጵያ መድን ፈተና እንደሚበዛበት መገመት ይቻላል።

ስምንት ጨዋታዎች ያከናወኑት አትዮጵያ መድኖች በአስራ ሦስት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ከንግድ ባንክ ጋር ነጥብ የተጋሩት መድኖች በውድድር ዓመቱ አንድ ሽንፈት ብቻ አስተናግደዋል። ለዚ ስኬት ትልቅ ድርሻ የሚወስደው ደግሞ በስምንት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ሲሆን በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመርም በጊዜ ሂደት ጥሩ ለውጦች ማምጣት ችሏል። ቡድኑ በነገው ዕለት በጨዋታ በአማካይ ከሁለት ግቦች በላይ ያስቆጠረ የወቅቱ የሊጉ ቁንጮ ግብ አስቆጣሪ ቡድን እንደመግጠሙ ከባለፉት መርሀ-ግብሮች የተለየ ፈተና እንደሚጠብቀው እሙን ነው።

ዝቅተኛ ሽንፈት ያስተናገዱ እና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኙ ክለቦች የሚያገናኘው የነገው ጨዋታ ውጤታማው የመቻል የፊት መስመር እና በቀላሉ የማይደፈረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የመከላከል አደረጃጀት መከከል የሚኖረው ፍጥጫም ትኩረትን የሚስብ ይሆናል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል አለን ካይዋ እና አብዲሳ ጀማል በጉዳት ዋንጫ ቱት ደግሞ በቅጣት አይኖሩም። ሚሊዮን ሠለሞን ግን ከቅጣት መልስ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው። በመቻል በኩል ያለው መረጃ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ከዚ ቀደም ለ15ኛ ጊዜያት የተገናኙት ክለቦቹ መድን በስምንቱ ጨዋታዎች ስያሸንፍ መቻል ስድስት ጊዜ ረቷል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ መድኖች 19 ግቦችን በማስቆጠር ሲመሩ መቻሎችም 18 ግቦች አሏቸው።

ስሑል ሽረ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ እና በመሀከላቸው የሁለት ደረጃዎች ልዩነት ያላቸው ቡድኖች በነገው ሁለተኛ መርሀ ግብር ይገናኛሉ። ሁለቱ ቡድኖች ከሰንጠረዡ ታችኛው ክፍል የሚያላቅቃቸው ድል ከዚህ ጨዋታ የሚያገኙ መሆኑ ሲታሰብ ፉክክሩ በጉጉት እንዲጠበቅ ያደርገዋል።

አሸንፎ ሊጉን በጥሩ ሁኔታ ከጀመረ በኋላ ለተከታታይ አራት ጨዋታዎች ሳይሸነፍ መዝለቅ ችሎ የነበረው ስሑል ሽረ በቅርብ ሳምንታት
መደነቃቀፍ አጋጥሞታል። ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ቡድኑ ካጋጠመው አሉታዊ ውጤት በመውጣት ከወራጅ ቀጠናው ለመላቀቅ በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያስፈልገዋል። በስሑል ሽረ በኩል ያለግብ ጨዋታን የማጠናቀቅ ጉዳይ ዋና ፈተናው ይመስላል። በሊጉ ካከናወናቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች በአምስቱ ግብ ሳያስቆጥር የወጣው ቡድኑ ኳስና መረብ ማገናኘት ከተሳነው ሦስት ጨዋታዎች አልፎታል።

ጥንካሬው ከጨዋታ ጨዋታ መቀነሱ ባይካድም እንደቡድን ያለው የመከላከል ቅንጅት አሁንም ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ሆኖም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያለው ችግር በነገው ጨዋታ ተሻሽሎ ሊቀርብ የሚገባው ዋነኛ ደካማ ጎኑ ነው።

አስር ነጥቦች ሰብስበው 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤት የሚያላቅቅ ድል ፍለጋ ስሑል ሽረን ይገጥማሉ።

በወራጅ ቀጠናው አፋፍ የሚገኘው ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግሞ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ከአደጋው ክልል ለመውጣት ድል ማድረግ አስፈላጊው ነው። በሦስት መርሀ-ግብሮች ስምንት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገድ የቻለው መቐለ የመከላከል አደረጃጀቱ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል። ቡድኑ የሚቆጠሩበትን ግቦችን መቀነሱም የዚ አንድ ማሳያ ነው፤ ሆኖም በመጨረሻው ጨዋታ ያስተናገዳቸው የጥቃቶች ብዛት ሲታይ አሁንም መሻሻል እንደሚኖርበት ጠቋሚ ነው።


እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ በምዓም አናብስቱ በኩልም ተመሳሳይ የፊት መስመር ችግር ይስተዋላል። በመጨረሻዎቹ አራት መርሀ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ የሚከተለው በመልሶ ማጥቃት ያማከለ አጨዋወት የወጥነት ችግር ይስተዋልበታል፤ በቅርብ ሳምንታትም በሚፈለገው የቅንጅት ደረጃ ላይ መድረስ አልቻለም። በነገው ዕለትም በቅርብ ሳምንታት የተሻሻለው የኋላው ክፍል ጥንካሬ ከማስቀጠል በዘለለ የማጥቃት አጨዋወቱ ደረጃ ከፍ የማድረግ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

በስሑል ሽረ በኩል ጋናዊው ተከላካይ ሱሌይማን መሐመድ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፍም። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ደግሞ ያሬድ ብርሀኑ፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያሉት መናፍ ዐወል እና ዮናስ ግርማይ እንዲሁም አብይ ተወልደ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ቡድኖቹ ከተሰረዘው እና በመቐለ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የ2012 ጨዋታ ውጭ በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 70 እንደርታ አንድ ጨዋታ ስያሸንፍ የተቀረው ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። መቐለ 3 ግቦች ስያስቆጥር ስሑል ሽረ 1 ግብ አስቆጥሯል።