በጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ መርሃግብር የብርሀኑ አዳሙ ብቸኛ ግብ ስሑል ሽረን አሸናፊ አድርጋለች።
ስሑል ሽረዎች ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ከተጋራው ቋሚ አሰላለፍ ክብሮም ብርሀነ እና አሌክስ ኪታታ በክፍሎም ገብረህይወት እና ጥዑመልሳን ሃይለሚካኤል ተክተው ሲገቡ
መቐለ 70 እንደርታዎች በበኩላቸው ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ብሩክ ሙልጌታ እና ያሬድ ብርሀኑ በኪሩቤል ሀይሉ እና ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ ተክተው ገብተዋል።
መቐለ 70 እንደርታዎች በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ግብ የተስተናገደበትም ገና በስምንተኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ዓብዱለጢፍ መሐመድ ከተከላካይ መስመር በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ አሻምቷት ሳጥን ውስጥ የነበረው ብርሀኑ አዳሙ በጥሩ ቅልጥፍና ከመረብ ያዋሃዳት ኳስም ስሑል ሽረን ቀዳሚ ያደረገች ኳስ ነበረች።
የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መያዝ ቢችሉም የጠሩ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ያልቻሉት ምዓም አናብስትም በቦና ዓሊ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ያሬድ ከበደ ከሰለሞን ሀብቴ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ አብርዶ አመቻችቷት ቦና ዓሊ መቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት ኳስም የተሻለች ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር እና የግብ ሙከራዎች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የመቐለ 70 እንደርታዎች ብልጫ የታየበት ነበር። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻለ ቢሆንም በቂ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻለም፤ ሆኖም መድሀኔ ብርሀኔ ከመስመር አሻግሯት ተመስገን በጅሮንድ ያደረጋት ሙከራ ፣ ያሬድ ከበደ ሰለሞን ሀብቴ ከመስመር አሻምቷት በግንባሩ ያደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ እና ተመስገን በጅሮንድ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ሞየስ ፖዎቲ ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራም ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብ የነበራቸው ስሑል ሽረዎችም በብርሀኑ አዳሙ አማካኝነት የግብ ልዩነቱን የሚያሰፉበት ዕድል አግኝተው ነበር። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን አሻሯት በግቡ አፋፍ ሆኖ ያመከናት ኳስም ወርቃማ የግብ አጋጣሚ ነበረች።
ጨዋታው በመጨረሻ ደቂቃዎች ብርቱ ፉክክር ቢደረግበትም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በስሑል ሽረ አሸናፊነት ተጠናቋል ፤ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የመቐለ 70 እንደርታ አምበል ያሬድ ከበደ የቀጥታ ቀይ ካርድ ተመልክቷል።