በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው ሀዋሳ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር በዛሬው ዕለት አመሻሹን በይፋ መለያየቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከምስረታው አንስቶ እየተወዳደሩ ከሚገኙ ሁለት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ ላለፉት ሦስት ዓመት ከግማሽ በፕሪምየር ሊጉ ላይ መቆየቱ ይታወሳል።
በያዝነው የ2017 የውድድር ዘመን ካደረጓቸው አስር ጨዋታዎች ውስጥ ሁለት በማሸነፍ ፣ ሦስት የአቻ ውጤት እና አምስት ሽንፈቶችን በማስተናገድ በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቦታ በሆነው 17ኛ ላይ ለመቀመጥ የተገደደው ቡድኑ በዚህ ውጤት የተነሳ የክለቡ ቦርድ በዛሬው ዕለት አመሻሹን እያደረገ በነበረው ስብሰባ ላይ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ውል ቢኖራቸውም ከአሰልጣኝነት እንዲነሱ ውሳኔን ስለ ማስተላለፉ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል። በአሁኑ ሰዓት አመሻሹን የክለቡ ቦርድ እያደረገ በሚገኘው ስብሰባ በቀጣይ አዳዲስ ውሳኔን ጨምሮ አዲሱ አሰልጣኝ ማን ሊሆን ይችላል የሚለውን የሚያሳውቅ ይሆናል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ የወልዋሎ አሰልጣኝ ከነበሩት አሸናፊ በቀለ በመቀጠል ከሊጉ የተሰናበቱ ሁለተኛው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ሆነዋል።