የውድድር ዓመቱ አጋማሽ የዝውውር መስኮት የሚከፈትበት ወቅት ታወቀ

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2ኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት መቼ እንደሆነ ተገልጿል።

የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመስከረም 10 ጀምሮ የዘንድሮውን ፍልሚያ በምስራቋ ሀገር ድሬዳዋ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በነገው ዕለት የ1ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐግብሩን አከናውኖ አጠቃላይ የድሬዳዋ ቆይታውን በማገባደድ ከብሔራዊ ቡድን የቻን ማጣሪያ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ተረኛ ከተማ ለማምራት በዝግጅት ላይ ይገኛል። የሊጉ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ለመገባደድ በጣት የሚቆጠሩ የጨዋታ ሳምንታት ቢቀሩም የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሊጉ የ2ኛው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት መቼ እንደሚከፈት ገልጿል።

በዚህም የሊጉ የሁለተኛው ዙር ውድድር መቼ እንደሚጀመር እስካሁን ባይታወቅም ፌዴሬሽኑ የዝውውር መስኮቱ ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ድረስ እንደሆነ አመላክቷል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት የሊጉ የበላይ አካል አውጥቼዋለው ባለው የተጫዋቾች ዝውውር እና የክለቦች ክፍያ አሰተዳደር መመሪያን በተመለከተ ከፍተኛ መነጋገሪያዎች የነበሩ ሲሆን ይህ ጉዳይ ማሰሪያ ሳያገኝ በመጪው የዝውውር ወቅትም መነጋገሪያነቱ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል።