መረጃዎች | 45ኛ የጨዋታ ቀን

ነገ በሚደረገው ተስተካካይ ጨዋታ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ሁለቱም ቡድኖች በወቅቱ በነበረባቸው የአህጉራዊ ውድድር ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ከ1ኛው ሳምንት በይደር የተያዘው ጨዋታ ነገ ይከናወናል።

ከሌሎች የሊጉ ክለቦች ያነሰ ጨዋታ ያከናወኑት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በዘጠኝ ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በሦስት ጨዋታዎች በእኩሌታ የአቻ እና የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበው ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ያሸነፉት ቻምፒየኖቹ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ለማምለጥ ሦስት ነጥቦች የማስመዝገብ ግዴታ ውስጥ ገብተው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

መርሐግብሩ ለንግድ ባንክ በጥሩ ጊዜ የመጣ አይመስልም። እስካሁን ሁለት ድሎችን ያሳካው ቡድኑ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻለም። አዞዎቹን በማሸነፍ ዓመቱን ቢጀምርም ዳግም ድል ለማድረግ ሦስት ጨዋታዎች ለመጠበቅ የተገደደው ቡድኑ በአምስተኛው ሳምንት ወልዋሎን መርታት ቢችልም በቀጣይነት ከመድን ጋር ያለግብ ተለያቶ እና በባህር ዳር ከተማ 3-0 ተሸንፎ በመጨረሻው መርሐግብር ደግሞ ከብርቱካናማዎቹ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ለነገው ጨዋታ ደርሷል።

የባለፈው ዓመት ጥንካሬውን ለማስቀጠል እየተቸገረ የሚገኘው ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በወጣበት ጨዋታ በብዙ ረገድ የተሻሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችልም አሁንም የግብ ማስቆጠር ችግሩ ቀጥሏል። አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ቡድናችው በድሬዳዋው ጨዋታው በአንፃራዊነት የተሻሉ የግብ ዕድሎች መፍጠሩ እንደ በጎ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐግብሮች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻለው የፊት መስመራቸው ላይ ማስተካከያዎች የማድረግ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።

በአስራ ሁለት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ አራት ደረጃዎች እንዲመነደጉ ይረዳቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች አገግሞ አርባ ምንጭ ከተማን ማሸነፍ ቢችልም በመጨረሻው ጨዋታ ከወልዋሎ ጋር ነጥብ የተጋራበትን ውጤት በማስመዝገብ ተስተካካይ ጨዋታውን ያደርጋል። ከቢጫዎቹ ጋር ባዶ ለባዶ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በሁሉም ረገድ ብልጫ የነበራቸው ቡናማዎቹ በጨዋታው ጉልህ የአፈጻጸም ክፍተት ተስተውሎባቸዋል። በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ አንድ ግብ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ በነገው ዕለት በመጨረሻው መርሐግብር ከወትሮ የተሻሻለ የመከላከል አደረጃጀት የነበረውን ንግድ ባንክ እንደ መግጠሙ የግብ ዕድሎችን በመፍጠርም ሆነ ግቦችን በማስቆጠር የተስተዋለበት ድክመት መቅረፍ ግድ ይለዋል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ኮንኮኒ ሀፍዝ ፣ በፍቃዱ ዓለማየሁ እና መላኩ አየለ አሁንም ከጉዳት ባለማገገማቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በንግድ ባንክ በኩልም ፉዓድ ፈረጃ፣ ሱሌይማን ሐሚድ እና ካሌብ አማንክዋህ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሆነዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 36 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 18 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ይዟል። ባንክ 9 ሲያሸንፍ በቀሪው 9 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 56 ጎሎች ፣ ባንክ 39 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል