ሪፖርት | አንተነህ ተፈራ ቡናማዎቹን ባለድል አድርጓል

አንደኛ ሳምንት ላይ መደረግ በነበረበት እና ዛሬ በተደረው ተስተካካይ የሊጉ መርሃግብር ኢትዮጵያ ቡና በአንተነህ ተፈራ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸንፈዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻ ጨዋታቸው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አዲስ ግደይን በዳዊት ዮሀንስ ምትክ ሲጠቀሙ በተመሳሳይ ከአቻ ውጤት የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ኤርሚያስ ሹምበዛ እና ስንታየሁ ዋለጬ እስወጥተው በምትካቸው ይታገሱ ታሪኩ እና ሲዲ ማታላን ተጠቅመዋል።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በምት ለተለየው አቤል መልካሙ (ዶ/ር) የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ በጀመረው ጨዋታው ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አማኑኤል አድማሱን እና አንተነህ ተፈራን በመጠቀም ከመስመሮች እየተነሱ አደጋ ለመፍጠር የሞከሩበት ነበር።

ቀስ በቀስ ተመጣጣኝ መልክን እየያዘ በመጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ለመያዝ ጥረት ቢያደርጉም በማጥቂያው ሲሶ ግን ዕድሎችን በጥራት ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ጨዋታው 38ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ ወሳኟን ግብ ከመረብ አሳርፈዋል ፤ በፈጣን ቅብብሎች ከግራ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ የደረሰውን ኳስ አንተነህ ተፈራ ተረጋግቶ በማስቆጠር አጋማሹ በቡናማዎቹ የበላይነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

በአንፃራዊነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበላይነት በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ በተሻለ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ተጠግተው ለመጫወት የሞከሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የተሻሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል ፤ በተለይም ኪቲካ ጅማ ያመከናት እንዲሁም አዲስ ግደይ ከቅጣት ምት በቀጥታ ሞክሯት የቡናው ግብ ጠባቂ በግብሩም ሁኔታ ያዳነበት ኳስ እጅግ አስቆጭ አጋጣሚዎች ነበሩ።


ምንም እንኳን መጠነኛ ብልጫ ቢወሰድባቸው አልፎ አልፎ ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን በመድረስ አደጋ ለመፍጠር የሞከሩት ቡናማዎቹ በእጃቸው የገባውን መሪነት አስጠብቀው ጨዋታውን በድል መወጣት ችለዋል።