በቅርቡ ከዋና አሰልጣኙ ጋር የተለያየው ሀዋሳ ከተማ በቀጣይነት ቡድኑን የሚመሩ ጊዜያዊ አሰልጣኞች ኃላፊነት ሰጥቷል።
ከውጤት ጋር በተያያዘ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ዓመታት ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ ከቆዩት ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር የተለያየው ሀዋሳ ከተማ የክለቡ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ ምክትል አሰልጣኞች በጊዜያዊነት እንዲመራ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ያለፉትን ጊዜያት የአሰልጣኝ ዘርዓይ ረዳት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ እና ብርሃኑ ወርቁ ቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ በቀጣይ ለሚያደርገው ጨዋታ ተጫዋቾችን እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተሰምቷል። ትናንት ቡድኑ ከዕረፍት መልስ ተሰባስቦ ልምምድ ሲጀምር በምክትል አሰልጣኞቹ እንደተመራም አውቀናል።
የክለቡ ቦርድ በቀጣይ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር በማሰብ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት የክለቡን አዲስ አሰልጣኝ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።