ሊጉ በቀጣይ በየትኛው ከተማ ይከናወናል?

አወዳዳሪው አካል በቀጣይ ሊጉ በአዲስ አበባ ወይም በአዳማ ከተማ እንደሚከናወን ቢገልፅም ሶከር ኢትዮጵያ በየትኛው ከተማ እንደሚከናወን ፍንጭ አግኝታለች።

የ2017 የውድድር ዘመን ከመስከረም ዘጠኝ ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ መከናወን ጀምሮ አስራ አንደኛው ሳምንት ላይ የድሬዳዋ ቆይታ መጠናቀቁ ይታወሳል። ምንም አንኳን እስከ አስራ ሶስተኛው ሳምንት ድረስ ውድድሩን በድሬዳዋ ለማጠናቀቅ አስቀድሞ መርሐግብር የወጣ ቢሆንም በድንገት ሳይጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የመጨረሻ ማጣርያ ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር ለሚያደርጋቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ዝግጅት ሲባል የመርሐግብር ማሻሻያ ማድረጉን ሊግ ካምፓኒው አሳውቋል።

ከ12ኛ ሳምንት ጀምሮ ያለውን ውድድር በአዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እና ታኅሣሥ 25 የሚጀምረውን 12ኛ ሳምንት በኋላ ያለውን መርሐግብር በቀጣይ ቀናት እንደሚያሳውቅም ጠቁሞ ነበር።

ሊግ ካምፓኒው ከሁለቱ ከተማ በአንዱ ከተማ ላይ ለማድረግ ከሚደረግ ጥረት ውጭ በየትኛው ከተማ እንደሚከናወን እስካሁን ማረጋገጫ ባይሰጥም ሶከር ኢትዮጵያ ከመረጃ ምንጮቿ ባደረገችው ማጣራት ከአስራ ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ያለው ውድድር በአዳማ ከተማ ለማድረግ የሚያስችል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አረጋግጣለች። በዋናነት ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች፣ የሕክምና መገልገያዎች እና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ከድሬዳዋ መጥተው አዳማ ከተማ እንዲቀመጡ የተደረገ ሲሆን የሜዳውን ሁኔታ የማዘጋጀት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አውቀናል። በዚህ መነሻነት እና ሌሎች ነገሮች ተደማምረው ሊጉ በቀጣይ በአዳማ ከተማ አስተናጋጅነት የመደረጉ ነገር የሰፋ ሆኗል።

ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖሩ መረጃዎችን ተከታትላ ወደ እናንተ የምታደርስ ይሆናል።