የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን አቻው ጋር የሚያደርገውን የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ጨዋታውን በዝግ ለማድረግ መታሰቡን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የመጨረሻ ማጣርያ ጨዋታውን ከሱዳን አቻው ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን አስመልክቶ ዛሬ በፌዴሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በመግለጫውም በሊቢያ ቤንጋዚ በሚደረገው ይህን ወሳኝ ጨዋታ ኢትዮጵያ ባለሜዳ የሆነችበትን ጨዋታ በዝግ ለማድረግ መታቀዱን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
አቶ ባህሩ በንግግራቸው“ ውድድሩ ሊቢያ ቤንጋዚ ላይ ነው የሚካሄደው አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በርካታ ሱዳናውያን በሊቢያ ኑራቸውን እያደረጉ እንደመገኘታቸው የሱዳን ቡድኖች በተለያዩ የካፍ ውድድሮች ላይ በስፍራው በተጫወቱበት ወቅት ሱዳናዊያን ተመልካቾች ሜዳው ሞልተው የሚታዩበት እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እየወሰድን ያለነው አቋም ጨዋታውን በዝግ ለማድረግ እንፈልጋለን። አካባቢውን ምቹ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ከካፍ ጋርም ንግግሮች እያደረግን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው። እኛ ባለሜዳ የምንሆንበት ጨዋታን ግን በዝግ ማድረጋችን የማይቀር ነው። በዝግ ሲባል ግን አንድ መታወስ ያለበት ነጥብ የተወሰነ ያህል የተጋጣሚ ቡድን አባላትን ወደ መቶ ሊቆጠሩ የሚችሉ ነፃ ትኬቶች ሊሰጡ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። በዚህ ደረጃ እኛም ውድድሩን እንፈልገዋለን። ማለፍም እንፈልጋለን ለማለፍ ደግሞ ምቹ የሆነ አካባቢ ለቡድናችን መፍጠር አለብን። ስለዚህ ጨዋታው በዝግ የመሆን ዕድሉ የሰፋ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እንፈልጋለን። በቀጣይ እነርሱ ባለሜዳ በሚሆኑበት ጨዋታ ግን ተመልካች ሊኖር ይችላል።” ሲሉ ተደምጠዋል።