ከነዓን ማርክነህ በመጀመሪያ ጨዋታው ግብ አስቆጥሯል

ኢትዮጵያዊው አማካይ የሊቢያ ሕይወቱን በግብ ጀምሮታል።

ከወራት በፊት መቻልን ለቆ ወደ ሊቢያው ክለብ አል መዲና ያመራው ኢትዮጵያዊ አማካይ ከነዓን ማርክነህ ለትሪፖሊው ክለብ የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል። ቡድኑ አል መዲና ትሪፖሊ አል ኢትሃድ አል ሚስራቲን ሦስት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ለክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ኢትዮጵያዊው በሰላሣ አምስተኛው ደቂቃ የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ያደረገች ግብ በማስቆጠር አጀማመሩን አሳምሯል።

በአራት ምድቦች ተከፍሎ በመካሄድ ላይ ባለው የሊቢያ ፕሪምየር ሊግ በምድብ አራት ላይ የሚገኙት አል መዲናዎች በመጀመርያው የሊግ ጨዋታቸው ከአሳርያ ጋር አቻ ቢለያዩም ዛሬ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል። ይህንን ተከትሎም ከከተማ ተቃናቃኛቸው አል አህሊ በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብለው በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል።