የቀድሞ ዋና ዳኛ የስራ ሽግሽግ እንዲያደርጉ ተደርገዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ዋና ዳኛ በመሆን ያገለገሉት እና ከወራት በፊት የወልቂጤ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን የተሾሙት የቀድሞ ዳኛ የስራ ሽግሽግ እንዲያደርጉ ተወሰነባቸው።


አስገዳጅ የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርት አለማሟላቱን ተከትሎ ከትልቁ የሊግ እርከን ዝቅ ብሎ እንዲሳተፍ ውሳኔ የተላለፈበት ወልቂጤ ከተማ 
በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ እየተሳተፈ ይገኛል ፤ እስካሁን ተስተካካይ ጨዋታቸውን ሳይጨምር በደረጃ ሰንጠረዡ አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሠራተኞቹ ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ የክለቡ አመራሮች ዋና አሰልጣኙን ሶሬሳ ካሚልን ከቡድኑ በማንሳት ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ የስራ ሽግሽግ መደረጉን የሚገልፅ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ችለናል ፤ ይህን ተከትሎ ቡድኑ ከቀናት በፊት ከቤንች ማጂ ቡና ጋር ያደረገውን ጨዋታ በቡድን መሪው አወል አማካኝነት እየተመራ ወደ ሜዳ መግባቱ ይታወቃል።

ታድያ ይህ ውሳኔ ያለስደሰታቸው አሰልጣኝ ሶሬሳ ካሚል ለደረሳቸው ደብዳቤ ምላሽ ሲሰጡ “ውሳኔው ተገቢ አይደለም በሁለት ዓመት ውል የተቀጠርኩት ለዋናው ቡድን አሰልጣኝነት እንጂ ተስፋ ቡድኑ ለማሰልጠን አይደለም።” ያሉ ሲሆን የስራ ሽግሽጉን እንደማይቀበሉ አያይዘው ደብዳቤ ለክለቡ ስለመቅላፃቸው አሳውቀውናል ፤ ሆኖም ለቅሬታቸወሰ ተገቢውን ምላሽ ካላገኙ ቅሬታቸውን ወደ ፌዴሬሽን ይዘው እንደሚሄዱ እንዲሁ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።