የዛሬው የጎረቤት ሀገራት ጨዋታን የሚመሩ አልቢትሮች ታውቀዋል

ዛሬ አመሻሽ 11 ሰዓት ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ በምስራቅ አፍሪካ ሀገር ዳኞች እንደሚመራ ታውቋል።

የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የመጨረሻ ዙር ማጣርያ ጨዋታዎች መደረግ የጀመሩ ሲሆን በዙሩ የመጀመርያ ጨዋታም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሱዳን አቻዋ ጋር ዛሬ አመሻሽ 11 ሰዓት በሊቢያ ቤንጋዚ ቤኒና ማርትየርስ ስታዲየም ታከናውናለች። ለዛሬ ጨዋታ በትናንትናው ዕለት (ለጨዋታው ከ29 ሰዓት በፊት) ስፍራው የደረሰው ብሔራዊ ቡድናችን ከአድካሚው ጉዞ በኋላ ጨዋታውን በሚያደርግበት ስታዲየም ከደረሰ ከሰዓታት በኋላ ልምምዱን ሠርቷል።

ለቻን ውድድር ከፊቱ 180 ደቂቃዎች ብቻ የሚቀሩት ቡድኑ ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሲያደርግ ዩጋንዳዊ አልቢትሮች ፍልሚያውን እንደሚመሩት ታውቋል። ላኪ ራዛቅ ካሳሊርዊ የጨዋታው ዋና አልቢትር ሲሆኑ ኢማኑኤል ኦኩድራ እና ካቴሬጋ አሽራፍ ረዳት እንዲሁም ጆርጅ ኦሌሙ አራተኛ ዳኛ ሆነው እንዲያገለግሉ ምደባ ተደርጓል።