በሄኖክ አዱኛ በግብጹ ክለብ መካከል የተፈጠረው ምንድን ነው?

ከወራት በፊት ለግብጹ ክለብ ሃራስ ኤል ሁዶድ ፊርማውን ያኖረው ሄኖክ አዱኛ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል።

የሊጉን ዋንጫ ደጋግሞ ከፍ ማድረግ የቻለው የመስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ ከወራት በፊት ነበር የሁለት ዓመታት ቆይታን ለማድረግ ፊርማውን በማኖር ወደ ግብጹ ክለብ ሃራስ ኤል ሁዶድ ያቀናው ፤ አሁን በሀገር ቤት የሚገኛው ሄኖክ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ በክለቡ እና በሄኖክ መካከል አለመግባባቶች እንደነበሩ ሰምተናል።

እንደ ወኪሉ አዛርያስ ተስፋጽዮን ገለጻ ከሆነ ሄኖክ በነበረው የሦስት ወር ቆይታ በስምምነቱ መሠረት ሊያገኘው የሚገባ የገንዘብ ክፍያ እንዳልተፈፀመለት እና በዚህም የተነሳ ጉዳዩን በህግ ለመፍታት ወደ ፊፋ ክስ መመስረታቸውን የገለፀ ሲሆን አያይዞም አሁን ላይ ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር መለያየቱን አረጋግጦልናል።

ወኪሉ ለሶከር ኢትዮጵያም እንዳረጋገጠው የሄኖክ አዱኛን አገልግሎት ለማግኘት የደቡብ አፍሪካ እና የኢራቅ ክለቦችን ጨምሮ በሀገር ቤት ያሉ የተለያዩ ክለቦች እርሱን ለመውሰድ ፍላጎት ስለማሳየታቸውም ለማወቅ ችለናል።