የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ስለብሄራዊ ቡድኑ ሽንፈት እና ቀጣይ ተስፋዎች ምን አሉ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ያደረጋቸውን ጨዋታዎች እና የነበረውን ቆይታ አስመልክቶ የቡድኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ከቀትር በኋላ ሰጥተዋል።

ብሄራዊ ቡድኑ በሁለቱም ጨዋታዎች ስለተሸነፈበት ምክንያት እና በጋዜጣዊ መግለጫው ” ተስፋ ሰጪ ነው” ብለው ስለገለፁት ነገር እንዲያብራሩ በጋዜጠኞች ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

” ስንሸነፍ ጉድለቶች ኖረው ነው የምንሸነፈው። አንዱ ከመከላከል ጋር በተገናኘ የነበሩ ክፍተቶች ናቸው እንድንሸነፍ ያደረጉት። ሌላው የምናገኝናቸው አጋጣሚዎች፤ አጋጣሚዎች አይደሉም ተደጋጋሚ የጎል ዕድል ነው ያባከነው። እነዛን ደግሞ የማታስቆጥር ከሆነ ትሸነፋለህ። ተደጋጋሚ የግብ ዕድል የምታባክን ከሆነ እዚህ ጋር ደግሞ በተለያዩ ድክመቶች ግቦች የሚቆጠሩ ከሆነ ምንም ጥያቄ የለውም ግብ ካላስቆጠርክ የፈጠርካቸው ክፍተቶች ደግሞ ባላጋራ ከተጠቀመ ትሸነፋለህ። እዛጋ ችግር አለብን። ግብ ማስቆጠር ላይ ክፍተቶች ነበሩ፤ ስንከላከልም ችግሮች ስለነበሩ ነው የተሸነፍነው።”


“በደምብ ነው ተስፋ የሚሰጥ ነገር ያለው። ምናልባት ጨዋታው በደምብ ማየቱ ጥሩ ነው፤ ዕድሉ ቢኖር ሁሉም ሰው ብያየው ብዬ ተመኝቻለው። አንደኛ ባላጋራ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳይችል አድርገን ነበር ስንሰራ የነበረው። ከዚያ ውጭ ደግሞ በቅርፅ ደረጃ ቅርፃችን እነሱ በፍፁም ”ማኔጅ’ ማድረግ የማይችሉት ቅርፅ ነው የነበረው።እነሱ 4-2-3-1 ነው የነበረው፤ የእኛ 3-4-3 ስለነበረ በፍፁም የኛን ተጫዋቾች ማቆም የሚችሉበት የቅርፅም የቁጥርም ሁኔታ አልነበረም።”

የኳስ ቁጥጥር ብቻ ቢሆን እንደዛ ላልል እችላለሁ። የነበረው እንቅስቃሴ ብዙ የግብ ዕድል መፍጠር፤ እነሱ እንዳይጫወቱ የማድረግ፤ አብዛኞቹ የእኛ ተጫዋቾች ክፍት ቦታ ይዘው ነበር ሲጫወቱ የነበረው ስለዚህ ይሄንን ጨዋታ ማሳደግ ብንችል ለብዙ ጥያቄ መልስ ይዞ ይመጣል ብዬ አስባለሁ። ውጤት ያስፈልጋል ለማሸነፍ ነው የተጫወትነው ግን ቅድም እንዳልኩት አንዳንድ ክፍተቶች ስላሉ ተሸንፈናል።” ሲሉ ተደምጠዋል።