መረጃዎች | 46ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሳምንታት ቆይታ በኋላ በነገው ዕለት ይመለሳል ፤ የአስራ አንድ ሳምንታት የድሬዳዋ ከተማ ቆይታው ያገባደደው ሊጉ ከነገ ጀምሮ ጨዋታዎቹን በአዳማ ከተማ የሚቀጥል ሲሆን የ12ኛው ሳምንት መክፈቻ መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች እና ሲዳማ ቡናዎች የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ነው።

በአስራ ሦስት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዞዎቹ ከሳምንታት በኋላ ያስመዘገቡትን ድል ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ሀዋሳ ከተማን አሸንፈው መጠነኛ እፎይታ ያገኙት አዞዎቹ በተመሳሳይ ነጥብ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ የተቀመጠውን የነገው ተጋጣሚያቸው ማሸነፍ የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።

በአራት ተከታታይ መርሃግብሮች አንድ ግብ ብቻ አስተናግዶ በጥሩ ብቃት የነበረው የአርባምንጭ ከተማ የኋላ ክፍል በ9ኛ እና 10ኛ ሳምንት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች መጠነኛ መንገራገጭ ገጥሞት ነበር። ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ  ባደረገው የመጨረሻው መርሃግብር ግን ከሳምንታት በኋላ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።

ይህም ከወሳኙ ድል በዘለለ ያስመዘገበው አንድ ጠንካራ ነጥብ ነበር ፤ በነገው ዕለትም በቅርብ ሳምንታት ጉልህ የፊት መስመር ድክመት እየተስተዋለበት ያለውን ቡድን እንደመግጠሙ ጠንካራ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም ተገማች እንዲሁም በግለሰቦች ጥገኛ የሆነው የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ለውጦች ማድረግ ይኖርበታል።

በመጀመርያዎቹ ሳምንታት አራት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ሊጉን እስከመምራት ደርሰው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በተደጋጋሚ ሽንፈቶች ደረጃቸው አሽቆልቁሏል። በአስራ ሦስት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ድል ካደረገ አምስት ሳምንታት ተቆጥረዋል። ከአሰልጣኝ ስንብቱ በኋላ በሚያደርገው የመጀመርያ ጨዋታም ከአዞዎቹ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል ተብሎ ይገመታል።

ሲዳማ ቡናዎች በሁሉም ረገድ አጥጋቢ የሆነ ብቃት ማሳየት አልቻሉም፤ ሆኖም እንዳላቸው የተጫዋቾች ጥራት እና ጥልቀት ውጤታማ መሆን ያልቻሉት የተከላካይ እና የፊት መስመር ክፍሎች የቡድኑ ዋነኛ ድክመቶች ናቸው።የፊት መስመሩ ለሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ከተሳነው በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሃግብሮች ሦስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ካለው የጥራት ደረጃ አንፃር አሁንም ደረት የሚያስነፋ ጥንካሬ ላይ አልደረሰም።

በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሃግብሮች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍልም በብዙ ረገድ መሻሻል ይገባዋል። የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ከመዋቅራዊ ድክመቱ በተጨማሪ ግለሰባዊ ስህተቶችም ይበልጥ ተጋላጭ አድርጎታል።

ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሃግብሮች ካስተናገዳቸው ስድስት ግቦች ውስጥ ሦስቱ መነሻቸው የተጫዋችቾ ስህተት መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ችግሩ መቀነስ ትልቁ የቡድኑ የቤት ስራቸው መሆኑ ጠቋሚ ነው።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት አበበ ጥላሁን እና ሳሙኤል አስፈሪ ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በተጨማሪም አሸናፊ ተገኝ እና ስቴፈን ባዱ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። የእንዳልካቸው መስፍን መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።
በሲዳማ ቡና በኩል ጊትጋት ኩት እና ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን ከቅጣት ሲመለሱ ብርሀኑ በቀለ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ18 ጊዜያት ተገናኝተው 12 ጨዋታዎች አቻ ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ 4 ሲዳማ ቡና ደግሞ 2 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ዐፄዎቹ እና ሀይቆቹ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ነው።

ከተከታታይ ድሎች በኋላ ነጥባቸው አስራ አራት አድርሰው 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ዐፄዎቹ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸው ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። 

ዐፄዎቹ ለሰባት ተከታታይ ሳምንታት ከድል ጋር በተራራቁበት ወቅት ለክፉ የማይሰጥ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችሉም የስነ-ልቦና ሁኔታቸው በበቂ ደረጃ ነበር ለማለት ግን ያዳግታል። በወቅቱ አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ጭምር የቡድናቸው ዋነኛው ችግር ስነ-ልቦናዊ እንደነበር መግለፃቸውም ይታወሳል። በቅርብ ሳምንታት ግን
በቡድኑ የታየው መንፈስ እና የድል ረሀብ ብዙ ነገሮች ቀይሯል። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ያሳዩት ተጋድሎ አንዱ ማሳያ ነው ፤ በነገው ጨዋታም ከዕረፍት በኋላ ይህንን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

ዐፄዎቹ ባለፉት ሁለት የሊግ መርሃግብሮች ግብ ባለማስተናገድ ጥሩ የመከላከል ቁጥሮች ማስመዝገብ ቢችሉም በማጥቃት ረገድ ግን አሁንም መሻሻል ይኖርባቸዋል። ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ አቻ እና ሁለት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገቡ እንደ በጎ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ግቦች ግን ሦስት ግቦች ብቻ ናቸው። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አሸናፊነቱ ለማስቀጠል በሚፈለገው መጠን ስል መሆን ያልቻለው የፊት መስመሩ ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ዓመቱን በድል ቢጀምሩም በተከታታይ የአቻ እና የሽንፈት ውጤቶች ደረጃቸው ያሽቆለቆለው ሀዋሳ ከተማዎች በዘጠኝ ነጥቦች ከሊጉ ግርጌ በአንድ ደረጃ ከፍ ብለው ይገኛሉ።

ከድል ጋር ከተራራቁ ስድስት መርሃግብሮች ያስቆጠሩት ሀይቆቹ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ በማሳካት በደካማ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። ይህንን ተከትሎም ከዋና አሠልጣኙ ዘርዓይ ሙሉ ጋር መለያየት ችለዋል።

ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መነቃቃት አሳይቶ በጨዋታዎቹ ብልጫ መውሰዱ ባይካድም ግብ የማስቆጠር ጉልህ ድክመት ተስተውሎበታል።
ክለቡ አሁን ከሚገኝበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የግድ ይለዋል። ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ደግሞ ግቦችን ማስቆጠር ይጠበቅበታል። 

በሊጉ በጨዋታ በአማካይ 0.7 ግቦች ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ የባለፈው የውድድር ዓመት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዓሊ ሱሌይማን ጨምሮ ለአዳማ ከተማ አስራ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ዮሴፍ ታረቀኝ ቢይዝም ሜዳ ላይ ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ታይቷል።

የቡድኑ ጉልህ የአፈፃፀም ችግር መፍታትም የአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ቀዳሚ የቤት ስራ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

በፋሲል ከነማ በኩል አፍቅሮተ ሰለሞን በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል፤ በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ የፊት መስመር ተሰላፊው ዮሴፍ ታረቀኝ ባልታወቀ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ስለማይገኝ በነገው ጨዋታ አይሳተፍም።

ሁለቱ ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በ15 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ዐፄዎቹ በአምስት ጨዋታዎች ድል በማድረግ ቀዳሚ ሲሆኑ ሀይቆቹ አራት ጊዜ አሸንፈዋል፤ ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል በጨዋታዎቹ ፋሲል 19 ሲያስቆጥር ሀዋሳ 20 ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።