ከ19 ቀናት በኋላ በተመለሰው የሊጉ ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሀብታሙ ታደሠ ብቸኛ ጎል አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 አሸንፏል።
በሲዳማ ክልል ቦና ወረዳ ከቀናቶች በፊት በደረሰው የመኪና አደጋ ህይወታቸው ላጡ ወገኖች የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኋላ በኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው እየተመራ ከአስራ ዘጠኝ ቀናት በኋላ የተመለሰው የሁለቱ ቡድኖች የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ይምሰሉ እንጂ ጨዋታው በአጠቃላይ ከፉክክር አኳያ ደካማ ነበር።
በይበልጥ ሲዳማ ቡናም ይሁን አርባምንጭ ከተማ ከመስመር መነሳትን መርጠው በሚያገኟቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ለመድረስ ያለመን እንቅስቃሴ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ብናይም የግብ አጋጣሚዎችን ጥራት ባለው መልኩ ተፈጥረው ከመመልከት ይልቅ በአመዛኙ የኃይል አጨዋወቶች ተበራክተውበት አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል።
ከዕረፍት ሲመለስ ሲዳማ ቡናዎች አንተነህ ተስፋዬ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በአስቻለው ሙሴ እና ማይክል ኪፕሮፕ በመለወጥ አጋማሹን በተሻለ መነቃቃት መጀመር ችለዋል። ወደ መስመር መዳረሻቸውን ባደረጉ ኳሶች ደጋግመው ሳጥን ውስጥ የሚገኙት ቡናማዎቹ 48ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሊመሩ ተቃርበው ነበር። ፍራኦል መንግስቱ ከቀኝ ለመስመር ካዘነበለ ቦታ የተገኘን ቅጣት ምት ወደ ውስጥ ሲያሻማ ግብ ጠባቂው ፋሪስ በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ ከግቡ የቀኝ ቋሚ ብረቱ ጋር ሆኖ ኳስን ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ በሚያስቆጭ መልኩ አጋጣሚዋን በቀላሉ አምክኗታል።
አህመድ ሁሴንን በሒደት ቀይረው ካስገቡ በኋላ ተጫዋቹን ያማከሉ እንቅስቃሴዎችን ያዘወተሩት አርባምንጮች ማጥቃቱ ላይ የቁጥር ብልጫን ባለ መውሰዳቸው በቀላሉ የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል ማስከፈቱ ከብዷቸው ታይቷል። ከመስመር አጨዋወት በተጨማሪ ረጃጅም ኳሶችን ወደ አጥቂ ክፍል በመጣል ብልጫውን እያሳዩ የቀጠሉት ሲዳማዎች 54ኛው ደቂቃ በዚሁ የጨዋታ መንገድ መስፍን ታፈሠ ከግብ ጠባቂው ፋሪስ ጋር በአንድ ለአንድ ግንኙነት ተገናኝቶ ብሩክ ባይሳ ከጀርባው ደርሶ ያስጣለው እና 60ኛው ደቂቃ ማይክል ኪፕሮፕ አክርሮ መቶ የግቡ አግዳሚ ብረት ከመለሠበት አጋጣሚ በኋላ 78ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል።
በረጅሙ ከራሳቸው ሜዳ የተጣለውን ኳስ የአርባምንጩ ተከላካይ አካሉ አትሞ በግንባር ማራቅ ተስኖት ኳሷን ፈጥኖ ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ በግሩም የመቀስ ምት ፋሪስ ዕላዊ መረብ ላይ አሳርፏታል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ምላሽ ለመስጠት ወደ ተቃራኒ ሜዳ ያመሩት አዞዎቹ በፍቃዱ መኮንን ያደረጓት ሙከራ በመስፍን ሙዜ ተመልሳባቸው ጨዋታውም በመጨረሻ በሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።