በ12ኛ ሳምንት የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን የምሽት ጨዋታ ዐፄዎቹ ከሀይቆቹ ጋር ጨዋታቸውን ያለግብ ነጥብ በመጋራት አጠናቀዋል።
ፋሲል ከነማ በ10ኛው ሳምንት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲን በመርታት ወደ እረፍት ካመራው የመጀመሪያ አስራ አንድ ምርጫቸው ውስጥ ሶስት ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ኢዮብ ማቲያስ፣ ሀቢብ መሐመድ እና ጃቢር ሙሉን ተክተው ሀብታሙ ተከስተ ፤ ዮናታን ፍሰሃ እና ተመስገን ካስትሮን ይዘው ሲቀርቡ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ከመጨረሻው ስብስባቸው ሲሳይ ጋቾ ፤ወንድማገኝ ማዕረግ እና ዮሴፍ ታረቀኝን በእስራኤል እሸቱ ፤ ፊቃደስላሴ ደሳለኝ እና እንየው ካሣሁን ተክተው ቀርበዋል።
አለመረጋጋቶች በበዙበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖቹ ኳስ ይዘው መጫወት ተስኗቸው የተስተዋሉ ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል በቀላሉ ኳሶችን ሲነጠቁ አስተውለናል።
በርከት ያሉ ቢጫ ካርዶች በተመዘዙበት እና ጉልበት የበዛበት በነበረው አጋማሹ ጨዋታው በጥፋቶች ምክንያት በተደጋጋሚም የተቋረጠበት ነበር።
በተደጋጋሚ በአደገኛ ስፍራዎች የቆመ ኳስ አጋጣሚዎችን ያገኙት ዐፄዎቹ ለግብ በ15ኛው ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ጥሩ የሚባልን አጋጣሚን መፍጠር ችለው ነበር ፤ ሀይቆቹ በአንፃሩ በረጃጅም ኳሶች ወደፊት ለመሄድ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በ32ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ከተሻማ ኳስ ሰለሞን ወዴሳ ያደረጋት ሙከራ ብቸኛ ዒላማውን የጠበቀች ሙከራ ነበረች።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የሀዋሳ ከተማው የመስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን በሰራው ጥፋት ከሜዳ በቀይ ካርድ ለመውጣት ተገዷል።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ፋሲል ከነማ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ተረጋግተው ኳስ መስርተው በመጫወት ረገድ ከተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ መውሰድ ችለዋል ፤ በዚህም የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉበት ቢሆንም በመጨረሻው ሲሶ የነበራቸው አፈፃፀም ግን አመርቂ አለመሆን ግብ ከማስቆጠር አግዷቸዋል።
ሀይቆቹ በአንፃሩ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በረጃጅም ኳሶች ለመጠቀም ጥረት ያደረጉ ሲሆን ምናልባትም በ80ኛው ደቂቃ ላይ ምናልባትም ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መቀየር ሚችሉበትን ወርቃማ ዕድል ቢያገኙም ዓሊ ሱሌይማን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በዚህም በብዚ መልኩ አሰልቺ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያለ አሸናፊ ተገባዷል።