መረጃዎች | 47ኛ የጨዋታ ቀን

የ12ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ይቀጥላሉ ፤ በዕለቱ የሚካሄዱትን መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ባህርዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በአንድ ነጥብ ልዩነት በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል የተቀመጡትን ቡድኖች የሚያገናኘው የነገው ጨዋታ አሸናፊውን ወደ መሪዎቹ የማስጠጋት አጋጣሚን ይዞ የሚመጣ እንደመሆኑ ተጠባቂ ነው።

በአስራ ስምንት ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ነጥብ ከተጋሩበት የመጨረሻው መርሀ-ግብር ለማገገም እንዲሁም ወደ መሪው ይበልጥ ለመጠጋት ድል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ከጨዋታ ጨዋታ ይበልጥ እየተዋሃደ እና እየጎለበተ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ በመጨረሻው መርሀ-ግብር በቅዱስ ጊዮርጊስ ተፈትኖ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ቢገደድም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ እንዳለ አይካድም። በተለይም በውድድር ዓመቱ አራት ግቦች ብቻ ያስተናገደው ጠጣሩ የመከላከል አደረጃጀት ቡድኑን አስፈሪነት አለብሶታል።

የነገው ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ከመሪው መቻል ቀጥሎ በርከት ያሉ ግቦች ያስቆጠረ ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን እንደመሆኑ በነገው ዕለት ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም ይበልጥ ሚዛናዊ እየሆነ የመጣው የቡድኑ አደረጃጀት የሚሰጠው ምላሽም የጨዋታውን መልክ ሊወስኑ ከሚችሉ ነጥቦች ዋነኛው ነው። 

ከወገብ በላይ የሚገኘው የፊት መስመር ጥምረትም የቡድኑ ሌላው ጠንካራ ጎን ነው ፤ ቀጥተኛ እንዲሁም በመስመር ተጫዋቾች ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድኑ ከሽንፈት በራቀባቸው ያለፉትን ስድስት መርሀ-ግብሮች ስምንት ግቦችን አስቆጥሯል። በነገው ዕለትም ከተጋጣሚያቸው የጨዋታ አቀራረብ አንፃር የተለመደው መንገድ ይመርጣሉ ተብሎ ይገመታል።

አስር ጨዋታዎች አከናውነው አስራ ስድስት ነጥቦች የሰበሰቡት ብርቱካናማዎቹ ከመሪው ጋር ያላቸውን የአምስት ነጥቦች ልዩነት ለማጥበብም ሆነ ባለበት ለማስቀጠል ከነገው ተጠባቂ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል።

ኳስን ለመቆጣጠር ታልሞ የተገነባው የብርቱካናማዎቹ ስብስብ አሁንም በጨዋታዎች ብልጫ ወስዶ በመጫወት ላይ ቢገኝም በውጤት ረገድ የወጥነት ችግር ይስተዋልበታል። ቡድኑ በሀድያ ሆሳዕና ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ከሽንፈት ቢርቅም  ያስመዘገባቸው ሁለት የአቻ ውጤቶች ወደ መሪው ይበልጥ እንዳይጠጋ እክል ሆነውበታል። ብርቱካናማዎቹ በጨዋታ በአማካይ 1.4 ግቦች ያስቆጠረው የሊጉ ሁለተኛ ምርጥ የፊት መስመር ጥምረት ዋነኛ ጠንካራ ጎናቸው ነው። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ እንደ ወትሮ ላቅ ያለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማስመዝገብ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢቸገርም አሁንም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።

በነገው ጨዋታ ተጋጣሚያቸው ይበልጥ በቀጥተኛ ኳሶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተከትሎ የለመዱት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማግኘት ይቸገራሉ ተብሎ ባይገመትም በሊጉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካላቸው አንዱ ከሆነው ቡድን የሚጠብቃቸው ፈተና በብቃት የመወጣት ፈተና ይጠብቃቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደው የመከላከል ጥምረቱም ጥንካሬውን ማስቀጠል ይኖርበታል።

የጣና ሞገዶቹ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስባቸው ይዘው ሲቀርቡ ብርቱካናማዎቹ መሐመድኑር ናስር እና ያሬድ ታደሰ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በድምሩ በሊጉ በአስር አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሶስቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲፈፀሙ ባህር ዳር ከተማዎች በስድስት ጨዋታዎች ባለድል ሲሆኑ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አንድ ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በጨዋታዎቹ ባህርዳሮች አስራ ዘጠኝ እንዲሁም ድሬዎች ደግሞ ሰባት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት አልተካተተም)

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ሁለት አንጋፋ የመዲናይቱ ክለቦች የሚያገናኘውን ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሀ-ግብር ነው።

ካከናወኗቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አስራ ሦስት ነጥቦች የሰበሰቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ከድል ጋር ለመገናኘት ከሌላው አንጋፋ የመዲናይቱ ክለብ ጋር ይፋለማሉ።

ፈረሰኞቹ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው በድል ማጀብ አልቻሉም። የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎች ማሳየት ቢችልም በጥቃቅን ስህተቶች ነጥብ ተጋርቶ ወይም ሽንፈት አስተናግዶ ለመውጣት ተገዷል።

በእርግጥ ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ጥቂት ግቦችል ያስተናገዱ የሊጉ ክለቦች የሆኑት ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን፤ የሊጉ መሪ መቻል፤ የአምናው ሻምፕዮን ንግድ ባንክ እና ጥሩ ስብስብ ያለው ሲዳማ ቡና የመሳሰሉ የሊጉ ጠንካራ ቡድኖች እንደ መግጠሙ ያስመዘገበው ውጤት ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ወደ ውጤት መመንዘር የሚያስችሉት ማሻሻያዎች ማድረግ ግድ ይለዋል። በተለይም የአፈፃፀም ክፍተቱ የቡድኑ ዋነኛ ክፍተት መሆኑ በመጨረሻዎቹ መርሀ-ግብሮች ተስተውሏል። በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሀ-ግብሮች መረቡን ካላስደፈረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሚደረገው የነገው ጨዋታም የግብ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ያለው ድክመት ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።

በተጨማሪም ከተጋጣሚያቸው አቀራረብ አንፃር የመልሶ ማጥቃት ተጋላጭነትን መቀነስ ተቀዳሚ ሥራቸው መሆን ይኖርበታል።

በውድድር ዓመቱ አንድ ሽንፈት ብቻ ከቀመሱ ሦስት ክለቦች አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሰንጠረዡ አጋማሽ ፈቀቅ ለማለት ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች መላቀቅ ግድ ይለዋል።

የኤሌክትሪኮች በውድድር ዓመቱ በስድስት ጨዋታዎች መረባቸው ባለማስደፈር ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት እንዳላቸው ብያስመሰክሩም
ጉልህ የግብ ማስቆጠር ችግር ይስተዋልባቸዋል።ቡድኑ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ካስቆጠረ በኋላ ከሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጋር በተደርጉ ጨዋታዎች አምስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሀ ግብሮች ያስቆጠረው የግብ መጠን አንድ ነው።
ቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግሩ በመሀል የቀረፈ ቢመልስም አሁንም ከባድ ስራ እንደሚቀራቸው እሙን ነው።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ አዘውትረው የሚጠቀሙበት ቀጥተኛ አጨዋወት ነገም ተመራጭ አቀራረባቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ፊት ተስቦ የሚጫወት እና የኳስ ቁጥጥር  የበላይነት ለመያዝ የሚታትር ቡድን መሆኑም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች የሚያገኙበት ዕድል እንዳለም ይገመታል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጉዳት ላይ የቆዩት አማኑኤል ተርፉ፣ ፍሪምፓንግ ኩዋሜ እና ባህሩ ነጋሽ ከጉዳት አገግመው ልምምድ የጀመሩ ቢሆንም የመሰለፋቸው ጉዳይ ግን ነገ ረፋዱን የሚለይ ይሆናል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ካመለጠው ተከላካዩ አብዱላሂ አላዮ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች 40 ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 በማሸነፍ  የበላይነትን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 3 አሸንፎ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 68 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ በበኩሉ 28 አስቆጥሯል።