በክረምቱ ሀዋሳ ከተማን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው ከክለቡ ጋር ለምን አይገኝም?
ባሳለፍነው የ2016 ክረምት ወር መጨረሻ ላይ ከተደረጉ ዝውውሮች መካከል ከአዳማ ከተማ ወደ ሀዋሳ ከተማ ያመራው የመስመር የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ዮሴፍ ታረቀኝ የዝውውር ሒደት በዐበይትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነበር። በአዲሱ ክለቡ መለያ በስድስት ጨዋታዎች 282 ደቂቃዎችን በሜዳ ላይ ግልጋሎትን የሰጠው የመስመር አጥቂ በአሁኑ ሰዓት ከክለቡ ጋር እንደማይገኝ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።
እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ሀዋሳ ከተማ በ11ኛው ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ 1ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ተጫዋቹ ከድሬዳዋ ከተማ ከክለቡ አባላት ጋር ሳይመለስ የቀረ ሲሆን ቡድኑም ዕረፍት ለተጫዋቾቹ ሰጥቶ ዳግም ወደ ልምምድ ሲመለሱ አጥቂው እንዳልተገኘ እንዲሁም በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ግልጋሎትን አለመስጠቱን ተከትሎ ለተጫዋቹ በተደጋጋሚ በክለቡ በኩል ጥሪ ቢቀርብለትም አሞኛል ብቻ በማለት እንደቀረ በኋላም ከተከታታይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች በኋላ የዕግድ ውሳኔን በተጫዋቹ ላይ በማስተላለፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ግልባጭ ማስገባቱንም ጭምር ሰምተናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ በተጫዋቹ በኩል የሚኖር ምላሽ ካለ በቀጣይ ይዘን የምንቀርብላችሁ ይሆናል።