ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ የጣናውን ሞገድ ሁለት ነጥብ አስጥለዋል

84 ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች በመጫወት ሲመሩ የቆዩት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከባህርዳር ከተማ ጋር 1ለ1 አጠናቀዋል።

ጠንከር ባለው የአዳማ ፀሀያማ ዐየር ታጅቦ በጀመረው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ያመረቁ እንቅስቃሴዎች ያልተደረጉበት ነበር። 6ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ ባህርዳሮች ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የተጣሉትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ለመጠቀም ጥረት በሚያደርግበት ወቅት የድሬዳዋ ከተማው የግብ ዘብ አብዩ ካሳዬ ከግብ ክልል ውጪ ኳስን በእጅ መንካቱን ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ በቀጥታ ቀይ ካርድ ተጫዋቹን ካስወጡት በኋላ በምትኩ አላዛር መርኔ ተክቶት ወደ ሜዳ ገብቷል።

ጨዋታው ሲቀጥል ወጥነትን አያሳዩ እንጂ ረጃጅም ሆነው ወደ መስመር በሚጣሉ ኳሶች የድሬዳዋ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ቶሎ ቶሎ ይገኙ የነበሩት ባህርዳሮች ከፍፁም ዓለሙ የቅጣት ምት ሙከራ በኋላ መሳይ አገኘሁ ከቀኝ ወደ ግብ ሲያሻማ ኳሷ የግቡን ቋሚ ለትማ የተመለሰችበት ምንአልባትም አደገኛዋ ሙከራ ነበረች።

ብዙም ብልጫውን ለመያዝ ጥረቶችን ውስን በነበሩበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ብርቱካናማዎቹ አንድ ተጫዋች ቢድልባቸውም ፈጠን ባሉ ሽግግሮች ሳይቸገሩ ማጥቃትን አልመው መንቀሳቀስ የቻሉ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ተጋጣሚያቸው የፈጠረባቸውን ጫና ተንተርሶ ግብ አስተናግደዋል። አጋማሹ ሊገባደድ በተሰጠው ጭማሪ 45+3 ደቂቃ ላይ ከቀኝ የተሻገረን ኳስ ወንድወስን በለጠ ጨርፎ ያቀበለውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ በይበልጥ ተመጣጣኝ ፉክክርን እንዲሁም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ደግሞ መጠነኛ መሻሻሎችን ያየንበት ነበር። ኳስን መሠረት ያደረጉ እና በአብዛኛው በቅብብሎሽ የታጀበው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ መነሻቸውን ከመስመር በማድረግ በጥልቅ መጫወትን መርጠው ቢታዩም ማጥቃቱ ላይ በቁጥር አንሰው መገኘታቸው በቀላሉ የሚያገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎች እንዳይጠቀሙ ዳርጓቸዋል።

በተወሰነ መልኩ የሰው ቁጥር ብልጫውን ቢይዙም በተጋጣሚያቸው ከመፈተን ያልዳኑት የጣናው ሞገድ ሙከራን በማድረጉ ግን ቀዳሚዎቹ ነበሩ። 61ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ያሻማውን ሙጂብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ ብረትን ገጭታ ኳሷ ለጥቂት ልትወጣበት ችላለች። ከጨዋታው አንዳች ነገርን ለማግኘት መታተራቸውን የቀጠሉት ብርቱካናማዎቹ 88ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ የአቻነት ግባቸውን አግኝተዋል።

መስዑድ መሐመድ መሐል ሜዳ አካባቢ የተገኘን ቅጣት ምት ወደ ሳጥን ሲያሻማ የግራው ቋሚ ብረት ጋር ቆሞ የተገኘው አህመድ ረሺድ ተጨራርፋ የደረሰችውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ፔፕ ሰይዶ መረብ ላይ በማሳረፍ በመጨረሻም ጨዋታው 1ለ1 በሆነ ውጤት እንዲቋጭ ሆኗል።