ፈረሰኞቹ በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠሩት ግቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ1 በመርታት ሶስት ነጥብ አሳክተዋል።
ፈረሰኞቹ በ11ኛው ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ አሰላለፍ ቶሎሳ ንጉሴ እና ፏአድ አብደላን በማሳረፍ ሄኖክ ዩሐንስ እና አብዱ ሳሚዮን ተክተው ሲገቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ10ኛው ሳምንት ከስሁል ሽረ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚያቸው በፊቃዱ አስረሳኸኝ አበባየሁ ዩሐንስ አቤል ሀብታሙ እና ቢኒያም በቀለን በማሳረፍ ሚኪያስ ካሣሁን፤ ሀብታሙ ሸዋለም ፤ኢዮብ ገ/ማርያም እና አባይነህ ፌኖን በቋምነት ይዘው ገብተዋል።
ግብ ገና በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች መቆጠር በጀመረበት በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ እየተፈራረቁ ብልጫ ለመውሰድ የጣሩበት ቢሆንም ፈረሰኞቹ በፈጣኝ ሽግሽግ ወደ ግብ ደርሰው ገና በአራተኛው ደቂቃ በግብ ማግባት ቀዳሚ ሆነዋል። በ4ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ጨርፏት የተሻገረችውን ኳስ ቢኒያም ፍቅሬ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ጋር በማገናኘት ፈረሰኞችን መሪ እንዲሆኑ አስችሏል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በእግራቸው ስር ሆኖ ደቂቃው ወደ አስራዎቹ መዳረሻ ቢደርስም የአቻነት ግብ ፍለጋ ያደረጉት ጥረታቸው ግብ ለማስቆጠረ አላስቻላቸውም። እንዲሁም በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደ ፈረሰኞቹ ግብ ክልል አዘውትረው ምንም እንኳ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል መድረስ ቢችሉም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማስመልከት አልቻሉም።
ወጥ የኳስ ንክኪ አቋም ባያሳዩም በፈጣኝ ሽግግር ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ክልል መድረስ የቻሉት ፈረሰኞቹ በ24ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛው ግብ በመረብ ላይ አሳርፈዋል። በግብ ክልል አከባቢ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ አብዱ ሳሚዮ ከግብ ሳጥን ውጪ ሆኖ አከርሮ በመምታት በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድጓል። አጋማሹም በፈረሰኞቹ ሁለት ግብ ብልጫ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ጠንከር ብለው የተመለሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ58ኛው ደቂቃ ላይ ኳስና መረብ አዋህደው የግብ ብልጫ ማጥበብ ችለዋል። ኢዮብ ገ/ማርያም የፈረሰኞቹን ተከላካዮች አታሎ በማለፍ ወደ ግብ ክልል ያሻማውን ኳስ አበል ሀብታሙ እንደምንም ደርሶ ጨርፏት ከመረብ ጋር ተገናኝታለች። ኢትዮ ኤሌክሪክ በድጋሚ በ66ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ አግንተው ወደ ግብ ተሻምቶ ያሬድ የማነ በግንባሩ ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ምናልባትም አቻ ለመሆን የቀረበ ሙከራም ነበር። ቡድኖቹ ግብ ለማስቆጠር ባላቸው ጉጉት የተነሳ አንዴ በአንድ ለአንድ ቅብብል በሌላኛው ግዜ ደግሞ በረጃጅም ኳሶች አደጋ መሆን ሚችሉበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።
የኤሌክትሪኮች ግብ መቆጠር ተከትሎ የጨዋታው ሂደት ተቀይሮ ግለቱን እየጨመረ ፉክክሩ ሳቢ እየሆነ እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ወደ ግብ መጠጋት የሆኑበትም ሆኗል። ፈረሰኞቹም የግብ ልዩነትን ለማስፋት በረጅም ኳስ ወደ ተጋጣሚው ቡድን ኳስ ይዞ መግባት የቻሉ ቢሆንም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨማሪ ግብ ላለማስተናገድ ጥንቃቄ አድርገው ኳሶችን በማራቅ በመጫወታቸው የግብ ማግባት ጉዳይ ሊሳካላቸው ሳይችል ቀርቶ ደቂቃው ወደ መገባደጃ ተቃርቧል። ለኢትዮ ኤሌክትሪክ በ86ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ሸዋለም በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተወገደበት አጋጣሚ ሲታወስ ቀሪውን ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል።
ሆኖም ግን ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት ፈረሰኞቹ 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል።