መረጃዎች | 48ኛ የጨዋታ ቀን

በ12ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ አዳማ ከተማ

በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታቸው በተመሳሳይ የአቻ ውጤት ፈፅመው ነገ የሚገናኙት ወልዋሎ እና አዳማ ከረጅሙ የሊጉ እረፍት በኋላ ድል አድርገው ደረጃቸው ለማሻሻል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ከተከታታይ ስምንት ሽንፈቶች በኋላ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው በመውጣት የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥባቸው ያሳኩት ወልዋሎዎች በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ አስመዝግበው ቀና ለማለት አዳማን ይገጥማሉ።

በሊጉ ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ በአንድ ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች እስካሁን ባስቆጠራቸው (2) ሆነ በተቆጠሩባቸው የግብ ብዛት (13) ስንመለከት ቡድኑ ስለምን በግርጌ እንደተገኘ ቁጥሮቹ በሚገባ ያስረዳሉ። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ደካማ የሆነው ቡድኑ በመጨረሻው መርሀ ግብር ለመጀመርያ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱ በጥሩ ጎኑ የሚነሳለት ጉዳይ ቢሆንም በማጥቃቱ ረገድ አሁንም ለውጦችን ይሻል።

ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያው ነጥብ ከማስመዝገቡም በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች የነበረበት የተነሳሽነት ችግር በመጠኑ ተቀርፎ ነበር፤ ይህም በነገው ዕለት ከቀደሙት ጊዜያት የተሻለ ግምት እንዲሰጠው የሚያደርግ ነጥብ ነው።

በመጨረሻው መርሀ-ግብር ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርተው የድሬዳዋ ቆይታቸው ያገባደዱት አዳማዎች የከተማቸው ቆይታ በድል ለመጀመር ወልዋሎን ይገጥማሉ።

በመጨረሻዎቹ አምስት መርሀ-ግብሮች አንድ ድል፣ ሦስት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ ከሽንፈት አልባው የአራት ተከታታይ ሳምንታት
ጉዞ በኋላ በወጥነት መዝለቅ ተስኖታል። ቡድኑ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ሁለት ለባዶ መምራት ቢችልም የኋላ ኋላ ሁለት ግቦች አስተናግዶ ነጥብ ለመጋራት ተገዷል።

በማጥቃቱ የነበራቸውን ጥረት እና አፈፃፀም ቡድኑ በነገው ጨዋታ ማስቀጠል የሚኖርበት ዋነኛው ጠንካራ ጎን ሲሆን በመከላከሉ ረገድ ግን የተመለከትናቸው ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ግድፈቶችን አርመው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ቡድኑ በነገው ጨዋታ በዘጠኝ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ ቡድን እንደመግጠሙ ፈታኝ የፊት መስመር ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም 14 ግቦች በማስተናገድ በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች ያስተናገደ ክለብ እንደመሆኑ ለወትሮ የመከላከል አደረጃጀቱ ማሻሻል ቀዳሚ የቤት ስራው መሆን ይኖርበታል።

በወልዋሎ በኩል አላዛር ሽመልስ እና ስምዖን ማሩ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤ አዳማ ከተማዎች በረዥም ጊዜ ጉዳይ ላይ ካለው ዳንኤል ደምሱ ውጭ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ለጨዋታው ይቀርባሉ።

በ2012 የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 4 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 2 ሲያሸንፍ፣ ወልዋሎ አንድ አሸንፎ ቀሪዋን አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይለዋል። አዳማ 5፣ ወልዋሎ 2 አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚታትሩትን ንግድ ባንኮችን ድል ከተረቡት መቐለዎች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሀ-ግብር ነው።

ሳይጠበቅ በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው ፉክክር የተገኘው ሻምፕዮኑ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ፤  በአራት ጨዋታዎች ሽንፈት በተቀሩት ሦስት ደግሞ ነጥብ በመጋራት ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስቦ በወራጅ ቀጠናው ይገኛል።

ንግድ ባንክ ምንም እንኳን 12ኛው ሳምንት በደረሰ ሊግ ዘጠኝ ጨዋታዎች ብቻ ብያከናውንም በውጤት ረገድ ያለበት አጠቃላይ  ቁመና አመርቂ አይደለም። ቡድኑ ማሸነፍ ባልቻለባቸው የመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ሁለቱን ብቻ ማሳካቱ እንዲሁም ከድል ጋር ከተራራቀ አራት የጨዋታ ሳምንታት ማስቆጠሩም አንድ ማሳያ ነው።

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ቡድኑ የሊጉን ክብር ባነሳበት የባለፈው ውድድር ዓመት ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ የነበረው የፊት መስመር ጥንካሬውን ማጣቱ ነው፤ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ባደረጋቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎችም ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖታል። በነገው ዕለትም የተጠቀሰው የግብ ማስቆጠር ጉልህ ድክመት መቅረፍ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ ያግዘዋል ተብሎ ይታመናል።

አስር ጨዋታዎች አከናውነው አስር ነጥቦች በመሰብሰብ በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል እያለው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በመጨረሻው ጨዋታ ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ በስሑል ሽረ ሽንፈት ያስተናገዱት መቐለዎች በጨዋታው በሁሉም ረገድ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም እንደ ወሰዱት ብልጫ በቂ የግብ ዕድሎች መፍጠር ባለመቻላቸው ለሽንፈት ተዳርገዋል። በአራት ተከታታይ ሳምንታት ሁለት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ጥሩ ጉዞ በማድረግ ላይ የነበረው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ተዳክሟል። በመጨረሻዎቹ አምስት መርሀ ግብሮች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ማሳካቱም የውጤት መንሸራተቱ ማሳያ ነው።

ቡድኑ በሦስት መርሀ-ግብሮች ስምንት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ በማስተናገድ በመከላከሉ ረገድ በጎ ለውጦች ማሳየት ቢችልም የማጥቃት አጨዋወቱ ውጤታማነት ወርዷል።በመጀመርያዎቹ አምስት ሳምንታት ከቡድኑ ውጤት በስተጀርባ ቁልፍ ሚናን የተወጣው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥራት በቀደመው ልክ ለመሆን መቸገሩም ለፊት መስመሩ መዳከም እንደ ምክንያት ማንሳት ይቻላል።

ቡድኑ በነገው ዕለት የተለመደው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ይተገብራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በርከት ያሉ ተጫዋቾች በጉዳት ማጣቱን ተከትሎ በአዳዲስ ጥምረቶች ወደ ሜዳ የሚገባበት ዕድል የሰፋ ነው።

በንግድ ባንክ በኩል ፉዓድ ፈረጃ ፣ ካሌብ አማንክዋ እና ሱለይማን ሀሚድ በጉዳት መሰለፋቸው አጠራጣሪ ሲሆን በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩልም  አምበሉ ያሬድ ከበደ በቅጣት፤ ያብስራ ተስፋዬ፣ ያሬድ ብርሀኑ፣ መናፍ ዐወል፣ ዮናስ ግርማይ፣ ኪሩቤል ኃይሉ፣ አሸናፊ ሀፍቱ እና አማኑኤል ልዑል ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱም ቡድኖች በነገው ዕለት በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።