በዕለቱ ቀዳሚው መርሃግብር አዳማ ከተማ በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን ወልዋል ዓዲግራት ዩኒቨርስቲን መርታት የከተማውን ቆይታ በድል ከፍቷል።
በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታቸው ከኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ነጥባቸውን የወሰዱት ወልዋሎዎች ለዛሬው ጨዋታ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ሱልጣን በርሄ እና አላዛር ሽመልስን አስወጥተው በምትካቸው ናትናኤል ዘለቀ እና ሰለሞን ገመቹን የተጠቀሙ ሲሆን በአንፃሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው የተመለሱት አዳማ ከተማዎች ከወላይታ ድቻ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ በተመሳሳይ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች አሸናፊ ኤልያስ እና ሙሴ ኪሮስ አስወጥተው በምትካቸው ፍቅሩ ዓለማየሁ እና ኤልያስ ለገሰን ተጠቅመው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
በብዙ መልኩ የተቀዛቀዘ አጀማመር በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሂደት ግን አዳማ ከተማዎች በእንቅስቃሴ ረገድ ብልጫን ወስደው መንቀሳቀስ ቢችሉም ብልጫቸውን በበቂ ሁኔታ ወደ ግብ ዕድሎችን ለመመንዘር ሳይችሉ የቀሩበት ነበር።
በተለይ አምበላቸው ፍቅሩ ዓለማየሁ በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል ተደጋጋሚ ስጋቶችን ለመደቀን ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል ፤ በአንፃሩ ወልዋሎዎች በአጋማሹ የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች መጠነኛ መነቃቃት ቢያሳዩም በአጋማሹ በአመዛኙ በሜዳ ላይ ግን የተገደበ እንቅስቃሴን ያደረጉበት ነበር።
በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ግን አዳማ ከተማ የሚገባቸውን መሪነት አግኝተው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ፤ 45ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ መሀል ሜዳ አካባቢ ከቡድን አጋሮቹ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ በአስደናቂ ፍጥነት ወደ ወልዋሎ ሳጥን እየነዳ በመግባት በግሩም አጨራረስ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
በንፅፅር የተሻለ ክፍት በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዳማዎች እንደ መጀመሪያው ሁሉ አንፃራዊ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን በዚህም በርከት ያሉ ግማሽ ዕድሎችን የፈጠሩበት ነበር።
ወልዋሎዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት በተወሰነ መልኩ የኳስ ቁጥጥር መጠናቸውን በማሳደግ እንዲሁም አውንታዊ ለውጦችን በመከወን ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው የታሰበውን ለውጥ ማምጣት ሳይችል ቀርቷል።
በ72ኛው ደቂቃ አዳማ ከተማዎች መሪነታቸውን አስተማማኝ ያደረጉበትን ግን አግኝተዋል ፤ ከግራ መስመር መነሻውን ባደረገው ማጥቃት በወልዋሎ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ኳሱ የደረሰው ነቢል ኑሪ በበረከት አማረ ስህተት ታግዞ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ያሳደገበትን ግብ አስገኝቷል።
ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኋላ በብዙ መልኩ ደካማ የጨዋታን እንቅስቃሴ ባስመለከተን ጨዋታ አዳማ ከተማዎች በጭማሪ ደቂቃ በኤልያስ ለገሰ አማካኝነት ተጨማሪ ግብን አክለው ጨዋታ በአዳማዎች የ3-0 አሸናፊነት ተደምድሟል።