ሪፖርት | የምሽቱ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

በሙከራዎች ያልታጀበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ 0ለ0 ተጠናቋል።

በፌድራል ዋና ዳኛ ሔኖክ አበበ አጋፋሪነት ጅምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ በፉክክር ብዙም መድመቅ ያልቻለ ቢሆንም በንፅፅር ግን ንግድ ባንኮች የተሻለውን ጊዜ አሳልፈዋል።

በፈጣን ሽግግሮች በአመዛኙ የተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ የሰነበቱት ሀምራዊ ለባሾቹ እንደነበራቸው አንፃራዊ ብልጫ ግን ጥራት ያላቸውን ዕድሎች መፍጠሩ ከብዷቸው ተስተውሏል።

11ኛው ደቂቃ በጥሩ ባሲሩ ዑመር አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ኪቲካ ተቀብሎ ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ግብ ቢመታም ሶፎኒያስ ሰይፈ ያወጣበት አጋጣሚ ምንአልባትም በአጋማሹ በልዩነት የምትነሳዋ የተሻለችው ሙከራ ነበረች።

ንግድ ባንኮች በቅብብል ወቅት የሚፈጥሯቸውን ስህተቶች ዋነኛ መነሻቸው አድርገው ለመጫወት የሞከሩት መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ መስመር ያጋደለ እንቅስቃሴ ቢኖራቸውም ይህ ነው የሚባል ነገርን በአጋማሹ አልፈጠሩም።

ጨዋታው ዝግ ባለ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲቀጥል ኪቲካ ጅማ ከርቀት መቶ የግብ ዘቡ ሶፎኒያስ የያዘበት እና ከተከላካይ ጀርባ ባሲሩ የጣለለትን ኳስ ኪቲካ በዝንጉነት ያመለጠችዋ እንዲሁም 39ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቢኒያም ጌታቸው ከግራ ኤፍሬም አሻግሮለት ነፃ ሆኖ ያገኘውን ኳስ በግንባር ገጭቶ በግቡ አግዳሚ ብረት በኩል ታካ የወጣችባቸው አጋጣሚ በንግድ ባንኮች በኩል በተከታታይ የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተደረገበት ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች በማጥቃቱ ረገድ ፍፁም ተዳክመው የታዩበት ነበር።

መዳረሻቸውን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ባደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በተመሳሳይ ቡድኖቹ ተጠቅመው ብናይም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎች ግን እምብዛም ያልነበሩበት አጋማሽ ነበር።

ጥፋቶች በይበልጥ የተበራከቱበት እና ተደጋጋሚ መቆራረጦች ያጠቁት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች በንግድ ባንክ በኩል 76ኛው ደቂቃ ቢኒያም ጌታቸውን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ሳይመን ፒተር ኪቲካ እንደምንም ታግሎ የሰጠውን ከሳጥኑ ቀኝ ቦታ መቶ ግብ ጠባቂው ሶፎኒያስ ያወጣበት እና 84ኛው ደቂቃ በመቐለ በኩል ክብሮም አፅብሃ ካመለጠችው ሙከራ በስተቀር ብዙም የፉክክር ግለት የራቀው ጨዋታ በመጨረሻም 0ለ0 ተቋጭቷል።