መረጃዎች | 49ኛ የጨዋታ ቀን

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ጨምሮ በገና ዋዜማ የሚካሄዱ የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሀ-ግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ስሑል ሽረ

ኢትዮጵያ መድን ደረጃው ለማሻሻል ስሑል ሽረ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።

ከዘጠኝ ጨዋታዎች አስራ አራት ነጥቦች ሰብስበው 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች የሰባት ደረጃዎችን መሻሻል ሊያስገኝላቸው የሚችል ወሳኝ ድል ፍለጋ ስሑል ሽረን ይገጥማሉ።

በውድድር ዓመቱ አንድ ሽንፈት ብቻ ከቀመሱ ሁለት ክለቦች አንዱ የሆነው መድን በነገው ዕለት በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ካስመዘገው የአቻ ውጤት ተላቆ ሦስት ነጥብ የሚያስመዘግብ ከሆነ ወደ 5ኛ ደረጃነት የሚመነደግበት ዕድል አለው፤ ይህንን ተከትሎም ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ከወትሮ በተለየ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይገመታል።

ኢትዮጵያ መድን የመከላከል አደረጃጀት አሁንም በአስደናቂው ጉዞው ቀጥሏል፤ ካከናወናቸው ዘጠኝ ጩዋታዎች በሰባቱ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ቡድኑ ሁለት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ጠጣር የመከላከል አደረጃጀቱ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ ነው።  እስካሁን ድረስ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ያላስተናገደው መድን የሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን(19) ካስቆጠረው የሊጉ መሪ መቻል በገጠመበት ጨዋታ የነበረው የመከላከል ጥንካሬ ቡድኑ ምንያህል ጠጣር እንደሆነ የታየበት ነበር።

በነገው ዕለትም በመከላከሉ ረገድ ፈታኝ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝለት ድል ለማግኘት በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ካስቆጠረባቸው መርሀ-ግብሮች በኋላ ኳስና መረብ ሳያገናኝ ከወጣበት የመጨረሻው ጨዋታ መልስ ወደ ግብ ማስቆጠሩ መመለስ ግድ ይለዋል።

መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ድል ያደረገው ስሑል ሽረ ነጥቡን አስራ አንድ በማድረስ በ14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በጨዋታው በመጨረሻዎቹ አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ካገኘው ድምር ነጥብ የላቀ ያገኘው ስሑል ሽረ ከነበረበት የውጤት ድባቴ የወጣ ይመስላል። ቡድኑ ከጨዋታው ወሳኝ ነጥብ ይዞ መውጣት ቢችልም የነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ተዳክሞ ተመልክተናል። በተለይም በዋነኝንነት በሽግግሮች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሚፈልገው የማጥቃት አጨዋወቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ 
እየተቀዛቀዘ ይገኛል።

ቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ የሆነው የመከላከል አደረጃጀት ብርታቱ ይዞ መቀጠል ቢችልም በነገው ዕለት ጥቂት ግቦች በማስተናገድ አናት ላይ የተቀመጠው እና የማይቀመስ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደመግጠሙ  የፊት መስመሩን በብዙ ረገድ አሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ዋንጫ ቱት በቅጣት አለን ካይዋ እና አብዲሳ ጀማል ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። ስሑል ሽረዎችም በነገው ጨዋታ ኬቨን አርጉዲ በህመም አዲስ ግርማ ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ነገ ይገናኛሉ።

መቻል ከ ሀድያ ሆሳዕና

በምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያገናኘው የሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ የ12ኛ ሳምንት መገባደጃ መርሀ-ግብር ነው።

በሀያ አንድ ነጥቦች ሊጉ በመምራት የሚገኙት መቻሎች መሪነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችላቸውን ድል ፍለጋ በሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይገመታል።

ላለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ሽንፈት አልባ ጉዞ ያደረገው እና በውድድር ዓመቱ በአንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈት የቀመሰው ጦሩ በጨዋታ በአማካይ 1.9  በድምሩ ደግሞ 19 ግቦች ያዘነበ ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት ገንብቷል። ቡድኑ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካለው መድን ጋር ባደረገው የመጨረሻ የሊግ ጨዋታው በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ኳስና መረብ ሳያገናኝ መውጣት ቢችልም አሁንም የሊጉ ምርጥ የፊት ጥምረት ያለው ቡድን ነው።

ጦሩ በነገው ዕለት ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ መረቡን ያስደፈረው እና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኝ ቡድን እንደመግጠሙ የሚጠብቀው ፈተና ከባድ ነው፤ ሆኖም ሦስት እና ከሦስት ግብ በላይ ያስቆጠሩ ሦስት ተጫዋቾች ያሉበት እና ተገማች ያልሆነው የማጥቃት አጨዋወታቸው በጨዋታው የተሻለ ግምት እንዲሰጠው ያስገድዳል።

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ተከታታይ ድሎች  ያስመዘገበው ሀድያ ሆሳዕና በምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል።


አስራ ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበው ከመሪው በሁለት ነጥቦች ርቀው በ3ኛ ደረጃነት የተቀመጡት ነብሮቹ በነገው ዕለት ተከታታይ የማሸነፍ ጉዟቸው የሚያቀጥሉ ከሆነ በሊጉ አናት ይቀመጣሉ። ቡድኑ በዘጠኝ ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሰ እና ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኝ ቡድን እንደመግጠሙ ከባለፉት መርሀ-ግብሮች የተለየ ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቀው እሙን ነው። ሆኖም  ካስመዘገቡት ውጤት ባሻገር  ያላቸው የድል ርሀብ እና ታታሪነት እንዲሁም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያሻሻሉት የፊት መስመር ጥንካሬም ቀላል ግምት እንዳይሰጣቸው ያደርጋል።

ለወትሮም ቢሆን በጠጣር አደረጃጀታቸው የሚታወቁት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ካለፉት አምስት
ጨዋታዎች በአራቱ ግቡን ያላስደፈረ አደረጃጀት ገንብተዋል፤ ድል ባደረገባቸው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው የፊት መስመርም በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሀ-ግብሮች አምስት ግቦች በማስቆጠር  በሂደት ወደ ጥሩ ብቃት መጥቷል።

ቡድኑ በነገው ዕለትም በድል አድራጊነቱ መቀጠል  ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን የሚያሰክርበት መሆኑም ጨዋታው ለቡድኑ ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።

የነገው ተጠባቂ ጨዋታ ቡድኖቹ በምርጥ ብቃት ላይ ከመገኘታቸው እና ከውጤት ፍላጎታቸው በተጨማሪ የደረጃ መቀያየር የሚያስከትልበት ዕድልም ስላለ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በመቻል በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት ነስረዲን ኃይሉ እና ዮዳሄ ዳዊት ቀለል ያለ ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። በሀድያ ሆሳዕና በኩልም ዝግጅት ላይ ባጋጠመው ጉዳት ለወራት ከሜዳ የራቀው እና በክለቡ መለያ የሊግ ጨዋታ ማከናወን ያልቻለው ጫላ ተሺታ ነገ የመጀመርያ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፤ በብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ጉዳት ያስተናገደው ተመስገን ብርሀኑ ግን ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ሲታወቅ የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ስምንት ጊዜ ተገናኝተው መቻል በአምስቱ የበላይነት ሲኖረው ሆሳዕና ሁለት አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። ጦሩ 12፣ ነብሮቹ 10 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።