ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ወደ መሪዎቹ ጎራ የተቀላቀለበት ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የ9፡00 ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ስሑል ሽረን ማሸነፍ ችሏል።

ኢትዮጵያ መድኖች ከመቻል ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ዳዊት ተፈራ እና በረከት ካሌብ በረመዳን ሑሴን እና መሐመድ አበራ ተክተው ሲገቡ ስሑል ሽረዎች መቐለ 70 እንደርታን ካሸነፈው ቋሚ ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ኢትዮጵያ መድኖች በኳስ ቁጥጥርም ይሁን ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ብልጫ ወስደው የተጫወቱበት የመጀመርያው አጋማሽ ስሑል ሽረዎች ወደ ራሳቸው ግብ ክልል ተጠግተው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ነበር። ሀይደር ሸረፋ ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው በመለሳት ኳስ ጥቃታቸው የጀመሩት መድኖች ወደ ሙከራነት ያልተቀየሩ ሁለት ጥሩ የግብ ዕድሎች መፍጠር ከቻሉ በኋላ በ 22ኛ ደቂቃ ጥረታቸው ሰምሮ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።
ወገኔ ገዛኸኝ ከመአዝን ምት አሻምቷት መሐመድ አበራ በግንባሩ ያስቆጠራት ኳስም መድን መሪ ያደረገች ኳስ ነበረች።

በአጋማሹ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ስሑል ሽረዎችም ምንም እንኳ በርከት ያሉ ሙከራዎች ማድረግ ባይችሉም በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ነበር። ብርሀኑ አዳሙ በግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ስህተት ያገኛትን ኳስ አግኝቶ መቷት ቋሚውን ለትማ የተመለሰች ኳስም የቡድኑ ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች።

በአጋማሹ ብልጫ የነበራቸው መድኖች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበት ዕድል ማግኘት ቢችሉም አልተጠቀሙበትም፤ መሐመድ አበራ በመልሶ ማጥቃት ይዟት የገባውን ኳስ ነፃ ለነበረው ሀይደር ሸረፋ አቀብሎት አማካዩ መቷት ሞየስ ፖዎቲ ያዳናት ኳስም የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማች በሁለቱም ቡድኖች ረገድ በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በአጋማሹ በሁሉም ረገድ ተሻሽለው የቀረቡት ስሑል ሽረዎች አሰጋኅኝ ጴጥሮስ ከቆመ ኳስ አሻምቷት አሌክስ ኪታታ በግንባር ካደረጋት ሙከራ በኋላ በ60ኛው ደቂቃ አቻ የምታደርጋቸው ግብ አስቆጥረዋል። አሌክስ ኪታታ፤ ብርሀኑ አዳሙ ከሳጥኑ የቀኝ መስመር ሰብሮ ገብቶ መቷት የግቡን ቋሚ ለትማ የተመለሰች ኳስ አግኝቶ ያስቆጠራት ኳስም ቡድኑን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ነበረች።

ሆኖም ኢትዮጵያ መድኖች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በረመዳን የሱፍ አማካኝነት መሪነታቸው ማስመለስ ችለዋል። ግብ አስቆጣሪው ረመዳን የሱፍ፤ አቡበከር ሳኒ ወደ ሳጥኑ አሻግሯት የስሑል ሽረ ተጫዋች የጨረፏትን ኳስ በቀላሉ ከመረብ ጋር በማዋሀድ ነበር ቡድኑን ወደ መሪነት የመለሰው።

ከግቧ በኋላ ሁለቱም ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች አምክነዋል፤ በስሑል ሽረዎች በኩል አብዱለጢፍ መሐመድ ከቆመ ኳስ አሻግሯት አሌክስ ኪታታ ያደረጋት ወርቃማ ሙከራ እንዲሁም በመድን በኩል መስፍን ዋሼ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ከግቡ በላይ የላካት ኳስ ይጠቀሳሉ።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ የደቂቃዎች ዕድሜ ሲቀሩት ግን ኢትዮጵያ መድኖች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ዳዊት ተፈራ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጫዋቾች ካለፈ በኋላ በግቡ አፋፍ የነበረው መስፍን ዋሼ ወደ ግብነት የቀየራት ግሩም ግብም የቡድኑን መሪነት ያጠናከረች ግብ ነበረች።

ጥሩ ፉክክር እና በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች የታየበት ጨዋታ በመድን አሸናፊነት መጠናቀቁ ተከትሎ ቡድኑ ደረጃውን ወደ አራተኛነት አሳድጓል።