የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ይጀምራል። የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ የሆኑ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ
በደረጃ ሰንጠረዡ የተለያየ ፅንፍ የሚገኙ ቡድኖች የሚያገናኘው መርሀ-ግብር የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ ነው።
በአምስት ጨዋታዎች ሽንፈት፤ በአራት ጨዋታዎች አቻ በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ድል አድርገው በአስር ነጥቦች ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት ሀይቆቹ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።
ሀይቆቹ ድል ካደረጉ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ተቆጥረዋል፤ ቡድኑ በአራት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ ቢጀምርም ከዛ በኋላ በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦች ብቻ በመሰብሰብ ደረጃቸው አሽቆልቁሏል። ለዚ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግር ነው። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖታት፤ ከዚ በተጨማሪም በሊጉ ግርጌ ከሚገኘው ወልዋሎ በመቀጠል ጥቂት ግቦች ያስቆጠረ ቡድን መሆኑም የግብ ማስቆጠር ችግሩ ምን ያህል ጉልህ ክፍተት መሆኑ ማሳያ ነው። ቡድኑ የባለፈው የውድድር ዓመት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዐሊ ሱሌይማን ጨምሮ ሌሎች ጥሩ የግብ ማስቆጠር ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች መያዝ ቢችልም ችግሩን መቅረፍ አልቻለም፤ በነገው ዕለትም በሊጉ በመከላከል ጥንካሬያቸው ከሚታወቁ ክለቦች አንዱ የሆነው ባህርዳር ከተማ እንደመግጠሙ ለሳምንታት የዘለቀው የግብ ማስቆጠር ችግሩ ለመፍታት ለውጦች ማድረግ ግድ ይለዋል።
በውድድር ዓመቱ አስራ ሁለት ጨዋታዎች ያከናወነ ብቸኛው የሊጉ ክለብ ባህርዳር ከተማ በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የጣና ሞገዶቹ ላለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ከሽንፈት ቢርቁም በመሀል በመሀል ነጥብ በመጋራት የጣሏቸው ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ከዚህም በላይ ከፍ እንዳይሉ አድርጓቸዋል።
በውድድር ዓመቱ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ቡድኑ በላይኛው ፉክክር ውስጥ ለመዝለቅ ከፈለገ በመሰል ጨዋታዎች ላይ ብልጫን ወስዶ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ሲታሰብ ደግሞ ከፉክክሩ ላለመረቅ ድል ማድረግ ግድ ይለዋል።
በመጨረሻው መርሀ-ግብር ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች መጫወቱን ተከትሎ ያገኘውን የቁጥር ብልጫ በአግባቡ መጠቀም ያልቻለው ቡድኑ ከሁለት መርሀ-ግብሮች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ በነገው ጨዋታ በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ይበልጥ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ የመቆየት ድፍረትን ተላብሶ መቅረብ ይኖርበታል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በሀዋሳ ከተማ በኩል ግን በረከት ሳሙኤል በአምስት ቢጫ ካርድ የነገው ጨዋታ በቅጣት የማይሰለፍ ሲሆን እንየው ካሣሁንም ከፋሲል ከነማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ ከነገው ጨዋታ ውጨ ሆኗል።
ባህር ዳር እና ሀዋሳ በሊጉ እስካሁን በ10 ጨዋታዎች የተገናኙ ሁለቱም ቡድኖች እኩል ሦስት ሦስት ጊዜ ተሸናንፈው በአራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። በግንኙነቱ ባህር ዳር ከተማ አስር ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ዘጠኝ ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሁለት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና የሚያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
በአስራ ሰባት ነጥቦች 5ኛ ደረጃነት ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከመሪው ጋር ያላቸውን የአምስት ነጥቦች ልዩነት ለማጥበብ ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
ከሊጉ መሪ መቻል በመቀጠል በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስቆጠር በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ ሦስት ግቦች አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው ግብ አንድ ብቻ ነው። ወሳኝ የፊት መስመር ተሰላፊው መሐመድኑር ናስር በጉዳት ያጣው ቡድኑ በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሀ-ግብሮች ስድስት የሊግ ግቦች ላስቆጠረው አጥቂ ሁነኛ ተተኪ በማበጀት የፊት መስመር ጥንካሬው ወደ ቀድሞ ብቃቱ መመለስ ይኖርበታል።
ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ሳያስደፍ በመውጣት ከዚ ቀደም በኳስ ምስረታ ሂደት እና የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች በመከላከል ረገድ የሚፈጠሩ ስህተቶች በመቅረፍ የመከላከል ችግሩ መፍታቱ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤት ተላቆ ዳግም ወደ ድል መመለስ ይኖርበታል።
በአስራ አምስት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቡናማዎቹ የአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሀ-ግብር በነበረው የመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው ያሳኩት ወሳኝ ድል ማስቀጠል የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።
ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በማገገም በሦስት መርሀ-ግብሮች ሰባት ነጥቦች የሰበሰበው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አልባ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛል። ቡናማዎቹ ካስመዘገቡት አወንታዊ ውጤት ባሻገር ለሳምንታት የቡድኑ አንዱ ችግር ሆኖ የቆየው የመከላከል ድክመት ቀርፈዋል። ከድሎቹ በፊት በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቶ የነበረው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱም የመከላከል አደረጃጀቱ መሻሻሉ ጠቋሚ ነው። በነገው ጨዋታም ምንም እንኳ አሁናዊ የማጥቃት ብቃቱ ደረት የሚያስነፋ ባይሆንም በሊጉ ሁለተኛው ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ ቡድን የሆነው ድሬዳዋ ከተማ እንደመግጠማቸው የኋላ መስመር ጥንካሬያቸው ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል መሐመድኑር ናስር በጉዳት አብዩ ካሳዬ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ መላኩ አየለ በጉዳት ምክንያት ለነገው ጨዋታ አይደርስም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 24 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 14 በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ይዟል። አምስት ጨዋታ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ድሬዳዋ 5 ጨዋታ አሸንፏል። ቡናማዎቹ 42፣ ብርቱካናማዎቹ 24 ጎሎች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)