ለተመልካች ሳቢ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ቡና የአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ከንግድ ባንክ ጋር አድርገው አንድ ለምንም በመርታት ወደ እረፍት ካመሩበት ቋሚያቸው አማኑኤል አድማሱ እና ሲዲ ማታላን በማሳረፍ በፍቃዱ አለማየሁ እና እስራኤል ሸጎሌን ተክተው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማ ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ከ12ኛው ሳምንት ቋሚያቸው አብዩ ካሣዬን እና አህመድ ረሸድን አስወጥተው ድልአዲስ ገብሬን እና አላዛር ማረንን ተክተው ገብተዋል።
ቡናማዎቹ ጫና ፈጥረው ቶሎ ቶሎ ወደግብ በደረሱበት በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በርከት ያለ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። ጨዋታው ከመጀመሩ ገና በሁለተኛው ደቂቃ እስራኤል ሸጎሌ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ አግኝቶ ወደግብ መጥቷት የብሩቱካናማዎቹ ግብ ጠባቂ በቀላሉ የተቆጣጠረው ሙከራ ሲታወስ ብርቱካናማዎቹ ግብ ክልላቸው አካባቢ ኳስ ነካክተው ወደፊት ለመሄድ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በሰሩት ስህተት በ5ኛው ደቂቃ ላይ ዲቫይን ዋቹኩዋ ስህተታቸውን ተጠቅሞ ወደሳጥን ይዞ በመግባት ጠንከር ያለ ሙከራ ቢያደርግም በተጠንቀቅ ሲጠብቅ የነበረው ግብ ጠባቂው አላዘር ማረን የመለሰበት አጋጣሚ ሌላኛው ከባዱ ሙከራ ነበር። ግብ ለማግባት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ብልጫ የወሰዱት ቡናማዎቹ በ16ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ቅብብል አንተነህ ተፈራ በተረከዝ ያሻገረውን ኳስ እስራኤል ሸጎሌ ከመረብ ጋር ቢያገናኝም ከጨዋታ ውጪ የተባለባቸው አጋጣሚ ይጠቀሳል።
ብርቱካናማዎቹም በአንፃሩ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ በተለየም በራሳቸው ሜዳ ኳስ ሲያንሸራሽሩ ቢሰተዋሉም ሁኔኛ ሙከራ ማድረግ ግን ተስኗቸዋል። ከ25ኛው ደቁቃ በኋላ ብርቱካናማዎቹ ኳስ ተቆጣጥረው በፈጣኝ አንድ ለአንድ ቅብብል የተሻለ ተንቀሳቅሰው ሙሉውን ብልጫ በመውሰድ እስከ ሰላሳኛው ደቂቃ መዳረሻ ድረስ ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ለተመልካች አስመልክተዋል።
በዚህም መሃል ቡናማዎቹ ኳስ ነጥቀው በፈጣኝ ሽግግር ወደ ብርቱካናማዎቹ ግብ ክልል መድረስ ላይ ቢያተኩሩም እንደመጀመሪዎቹ ደቂቃዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም። ይልቁንስ ይዘው ሚገቡትን ኳሶች በአግባቡ መጠቀም ተስኗቸው ቆይተዋል። በ40ኛው ደቂቃ ላይ ኪሩቤል ደሳለኝ ያለቀ ኳስ ከተከላካይ ጀርባ በመጣል ለአንተነህ ተፈራ አሻግሮለት አንተነህ ተፈራ መረጋጋት ተስኗት ኳሱን ሳይቆጣጠር ቀርቶ ኳስ ወደውጪ የወጣበት አጋጣሚ ለቡናማዎቹ ምናልባትም በአጋማሹ የግብ ብልጫ ወስደው ወደመልበሻ ክፍል መግባት የሚያስችላው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። በዚህም አጋማሹ ያለግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ሲመለስ ብርቱካናማዎቹ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረው በመጫወት ስራ ተጠምደው ብልጫ ለመውሰድ ጥረት በማድረግ አለፈው አለፈውም የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በ69ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካናማዎቹ ካደረጓቻቸው ሙከራዎች የተሻለውን ሙከራ አድርገዋል። ዘረዓይ ገብረስላሴ ከሳጥን አጠገብ የመታው ኳስ ከግቡ ግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ያለፈበት ሙከራ ለግብ የቀረበ አደገኛ ሙከራ ነበር። ቡናማዎቹም በአንፃሩ በፈጣኝ ኳስ ቅብብል ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን አድርገዋል።
በ63ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ኪሩቤል ደሳለኝ ወደግብ አሻምቶት አንተነህ ተፈራ በግንባሩ ገጭቶ ለትንሽ ያለፈበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሙከራም ነበር። የግብ ሙከራዎቻቸውን በጋለ ሁኔታ የቀጠሉት ቡናማዎቹ በእስራኤል ሸጎሌ አማካኝነት አከታትለው ያገኙትን የግብ ማግባት ሙከራዎች ዒላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተው አጋጣሚዎቹን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። እንዲህ እያለ ደቂቃው ወደ መገባደጃ ሲቃረብ በ81ኛው ደቂቃ በአንተነህ ተፈራ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በሚል ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሰ ፍፁም ቅጣት ምት ለኢትዮጵያ ቡና ሰጥተው ዋና ዳኛው ሄኖክ አክሊሉ የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔውን በመቀበል በፊሽካቸው ቢያረጋግጡም ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ረዳት ዳኛው እና ዋና ዳኛው በመነጋገር የፍፁም ቅጣት ምቱን ሊሽሩት ችለዋል። መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው በ93ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል አድማሱ ከመሃል በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ይዞ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊትለፍት ተገናኝቶ በጨዋታው ጥሩ በመንቀሳቀስ በርከት ያሉ ኳሶችይ ማዳን የቻለው ግብ ጠባቂው አላዛር ማረን በቅጥፍና መልሶበት ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ ተገዷል።