በድራማዊ የመጨረሻ ደቂቃ ትዕይንቶችን ባስመለከተን የምሽቱ ጨዋታ ፈረሰኞቹ አዳማ ከተማን መርታት ችለዋል።
አዳማ ከተማ በ12ኛው ሳምንት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲን ከረቱበት ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ፈረሰኞቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ካሸነፉበት ቋሚ አሰላለፍ አማኑኤል ተረፉ እና ፍፁም ጥላሁንን በፍሪምፖንግ ከዋሜ እና ድግማዊ አርአያን ተክተው የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል።
በፈጣን ሽግግሮች ታጅቦ ሳቢ የጨዋታ እንቅስቀሴን ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴን ከማድረግ ባለፈ የበርካታ ደጋፊዎች ሜዳ መገኘት ጋር ተዳምሮ እጅግ ማራኪ ፉክክር አስመልክቷል።
ፈረሰኞቹ በአጋማሹ አደገኛ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ መውሰዱ ሲችሉ በ11ኛው ደቂቃ ላይ ዳግማዊ አርዐያ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ወደግብ በመምታት ያደረገው ሙከራ ለትንሽ ከግብ ቋሚ በኩል ያለፈበት አጋጣሚ እንዲሁም በ18ኛው ደቂቃ ላይ ዳግማዊ አርዓያ በግራ መስመር በኩል ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነው አጋጣሚ ሌላኛው ለፈረሰኞቹ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። እንዲሁም በ24ኛው ደቂቃ ላይ በአማኑኤል ኤርቦ ላይ በተሰራ ጥፋት አደገኛ ቦታ ላይ ቅጣት ምት አግንተው አብዱ ሳሚዮ በግሩም ሁኔታ ቀጥታ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ የግብ ቋሚ የመለሰባቸው አጋጣሚ የፈረሰኞቹ ተጠቃሽ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ።
በአጋማሹ አዳማ ከተማ በአንፃሩ ኳስ ይዘው ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ደርሰው አደገኛ የሚባል የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
በ43ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው ኤልያስ ለገሰ በርቀት አክርሮ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ለትንሽ ከቋሚ ብረት ርቃ ያለፈችው አጋጣሚ የአዳማ ከተማዎቹ ለግብ የቀረበ አደገኛ ሙከራ ነበር።
ከእረፍት መልስ አዳማ ከተማዎች ጠንከር ብለው በመመለስ ቶሎ ቶሎ ወደ ፈረሰኞቹ ግብ ደርሰው ጫና አሳድረዋል። በ58ኛው ደቂቃ ላይ ነቢል ኑሪ ኳስ ይዞ ወደ ሳጥን በመግባት ተጫዋቾችን ቀንሶ ያለቀ ኳስ ለስንታየሁ መንግስቱ አቃብሎት ወደ ግብ ቢመታም የፈረሰኞቹ ተከላካዮች ተረባርበው ያዳኑበት ኳስ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።
ፈረሰኞቹም በረጅምና በአጫጭር ኳሶች አስከትለው ጥሩ ተንቀሳቅሰው ሙከራዎችን አድርገዋል። ሆኖም ግን እንደመጀመሪያው አጋማሽ ጫና አሳድረው ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ደርሰው አደገኛ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ተመልክተናል ፤ ይልቁንስ የሚያገኙትን አጋጣሚዎች በደካማ አጨራረስ በማምከን በግብ ማግባት ሙከራዎች ብልጫ ተወስዶባቸው ሰንብተዋል።
ጨዋታው ቀጥሎ 80ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከማዕዘን ተሻምቶ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች ለማራቅ ጥረት በሚያደርጉበት ቅፅበት ከሳጥን ውጪ ሆኖ ሲጠባብቅ የነበረው በረከት ወልዴ በግሩም ሁኔታ ጠንከር ያለ ኳስ ወደግብ መጥቶ ከግብ ቋሚ ለትንሽ ከፍ ብሎ ያለፈበት አጋጣሚ ይታወሳል። አዳማ ከተማ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው ገብተው ነቢል ኑሪ ከግብ ጠባቂ ፊትለፍት ተገናኝቶ ሳይጠቀም ቀርቶ ኳሱ በረጅሙ ወደ ሶስተኛው ክፍል ደርሶ ፈረሰኞቹ ወደግብነት ቀይረውት መሪ መሆን ችልዋል።
በ83ኛው ደቂቃ የአዳማ ከተማው ተከላካይ በሰራው ስህተት አማኑኤል ኤርቦ ኳስ ቀምቶ እየገፋ ይዞ በመግባት በቀላሉ ከመረብ ጋር አገናኝቶታል።
ግቧ ከተቆጠረች በኋላ የእለቱ ዋና ዳኛና ረዳት ዳኛ መካከል አለመግባባቶች ተፈጥረው ጨዋታው ቢቆረጥም የኋላ ኋላ ግቡ ፀድቆ ጨዋታው መቀጠል ችሏል። ጨዋታው ቀጥሎ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ ደቂቃ በታየው አዳማ ከተማዎች የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል።
92ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ከመሃል ሜዳ አከባቢ አሸናፊ ኤልያስ ወደ ግብ አሻምቶ ስንታየሁ መንግሰቱ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ አቻ እንዲሆኑ አስችሏል።
ጭማሪ ደቂቃዎች ሊጠናቀቁ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት ተገኑ ተሾመ ለፈረሰኞቹ የማሸነፊያ ግብ መረብ ላይ አሳርፏል። የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂና ተከላካይ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት የተገኘውን ወርቃማ አጋጣሚ ወደ ግብ ቀይሮ ለፈረሰኞቹ በተጨማሪ ደቂቃዎች ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስጎንፅፏል።