በ13ኛው ሳምንት የ3ኛ ቀን ውሎ የመጀመርያ ጨዋታ መቻል ስሑል ሽረን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል
ስሑል ሽረዎች በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ ሞየስ ፖዎቲ፣ ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል እና መሐመድ ዓብዱልለጢፍ በፋሲል ገ\ሚካኤል፣ መሐመድ ሱሌይማን እና አሌክስ ኪታታ ተክተው ሲገቡ መቻሎች በበኩላቸው በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ከገጠመው ቋሚ በኃይሉ ግርማ በዳንኤል ዳርጌ ተክተው ገብተዋል።
ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ባደረጉት ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢጀምርም መቻሎች ብዙም ሳይቆዩ ብልጫ ወስደው የተጫወቱበት ነበር። የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይዘው የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም በረከት ደስታ መቷት ግብ ጠባቂው ከመለሳት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ንፁህ ሙከራ ሳያደርጉ የቆዩት መቻሎች በ24ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ ሽመልስ በቀለ ከምንይሉ ወንድሙ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ አክርሮ በመምታት ያስቆጠራት ኳስም ጦሩን መሪ ማድረግ የቻለች ግብ ነች።
መቻሎች ከግቧ በኋላም በሽመልስ በቀለ እና ዳንኤል ዳርጌ አማካኝነት ሙከራዎች ካደረጉ በኋላ ተከላካዩ ግሩም ሀጎስ ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን ማጠናከር ችለዋል። ተከላካዩ ሽመልስ በቀለ ከመአዝን ምት ያሻማትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ነበር ግቧን ያስቆጠራት።
ጥሩ አጀማመር ማድረግ ቢችሉም የኋላ ኋላ የተዳከሙት ስሑል ሽረዎችም በፋሲል አስማማው እና ነፃነት ገብረመድኅን አማካኝነት ሙከራዎች አድርገዋል፤ በተለይም ነፃነት ከቆመ ኳስ የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።
ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እና ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ቢሆንም ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በረከት ደስታ ከርቀት አክርሮ መቷት የስሑል ሽረው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል በምያስደንቅ ሁኔታ በመለሳት ሙከራ የጀመረው አጋማሹ በሀምሳ ሦስተኛው ደቂቃ ግብ ተስተናግዶበታል።
አስቻለው ታመነ፤ ጃዕፈር ሙደሲር ከቆመ ኳስ ካሻማት በኋላ በግንባር የተገጨችውን ኳስ ለማውጣት በሚያደርገው ጥረት ወደ ራሱ ግብ ያስቆጠራት ኳስም ስሑል ሽረን ወደ ጨዋታው የመለሰች ኳስ ነበረች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ስሑል ሽረዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩበት ሲሆን በሙከራ ረገድ ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥቂት ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። የመቻሉ ዳንኤል ዳርጌ ከሳጥኑ ግራ ክፍል ሆኖ ያገኛት ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል የመለሳት ኳስም የተሻለ ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።