ሪፖርት | የሲዳማ ቡና እና ንግድ ባንክ ጨዋታ ያለ አሸናፊ ተጠናቋል

በሁለቱ አጋማሾች የተቆጠሩ ሁለት ግቦች ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ነጥብ አጋርተዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከአምስት የ90 ደቂቃዎች ጥበቃ በኋላ ከድል ጋር የተገናኙበትን ውጤት አርባምንጭ ከተማ ላይ የተቀዳጁት ሲዳማ ቡናዎች ”አሸናፊ ቡድን አይቀየርም” በሚል መርህ ይመስል አንድም ተጫዋች ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያለ ጎል የተለያዩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደግሞ አምበላቸው ፈቱዲን ጀማልን እና አጥቂው ሲሞን ፒተርን በዮናስ ለገሰ እና ቢኒያም ጌታቸው ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

በፈጣን ቅብብል የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደራሳቸው በማድረግ መንቀሳቀስ የጀመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች መሪ ለመሆን ከ7 ደቂቃዎች በላይ አልፈጀባቸውም። በዚህም በራሳቸው የግብ ክልል የተሰጠባቸውን የቅጣት ምት በእርጋታ በማምከን በድንቅ የቡድን ስራ እና በፈጣን ሽግግር ወደ ሲዳማ የግብ ክልል በማምራት በጊዜ መሪ የሆኑበትን ግብ በሳይመን ፒተር አማካኝነት አግኝተዋል።

ዘለግ ያለውን ደቂቃ ከኳስ ጀርባ በመሆን እያሳለፉ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች የተደራጀ ባይሆንም በመጀመሪያው አጋማሽ አካፋይ ደቂቃ ድረስ ሁለት ጊዜ ፓላክ ቾልን ጎብኝተው ተመልሰዋል። ቀስ በቀስ ግን በጨዋታው እያደጉ ቢያንስ የተወሰደባቸውን የጨዋታ ቁጥጥር ወደ ራሳቸው በማድረግ ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን የመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ ደርሶ አስደንጋጭ ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን ውስንነቶች ነበሩባቸው። በተቃራኒው ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተለየ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ እየተዳከሙ የመጡት ንግድ ባንኮች ብቸኛዋን የአጋማሹ ጎል አስጠብቀው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና ጥቂት የጎል ሙከራዎች በታዩበት ሁለተኛ አጋማሽ ባንኮች ከቆሙ ኳሶች አደጋ ሲፈጥሩ ሲዳማዎች በአንድ ሁለት ቅብብል እድሎች ለመፍጠር ሞክረዋል። ከቀኝ መስመር ኤፍሬም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ተመስገን ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው መስፍን የመለሰበት ኳስ የባንክን መሪነት ለማስፋት የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

61ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች የአቻነት ጎል አግኝተዋል። ሀብታሙ ታደሰ ከደስታ የመጣለትን ኳስ ወደ ፊት ሲያሻግር የባንክ ተከላካይ እንዳለ ዮሐንስ ኳሷን ለማራቅ ሲሞክር አምልጦት ኳስ መስፍን ታፈሰ ጋር የደረሰ ሲሆን መስፍንም በጥሩ አጨራረስ ሲዳማ ቡናን አቻ አድርጓል።

ሲዳማዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ የሚችሉበት እድል አግኝተው ነበር። ሀብታሙ ታደሰ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው ኳስ አግዳሚውን ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ተደጋጋሚ የቅጣት ምቶችን በሲዳማ አጋማሽ ያገኙት ባንኮች በ85ኛው ደቂቃ ጥሩ እድል በድጋሚ አግኝተዋል። ኤፍሬም ታምራት ያሻማውን ኳስ ባሲሩ ዑመር በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው መስፍን አውጥበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ አንድ ለአንድ ተጠናቋል።