መረጃዎች | 53ኛ የጨዋታ ቀን

የ13ኛ ሳምንት መገባደጃ የሆኑ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ

መሪነቱን ለመቆናጠጥ እያለሙ ወደ ሜዳ የሚገቡት ነብሮቹ ከዐፄዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ስድስት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ አስደናቂ ጉዞ ላይ በማድረግ የሚገኙት ነብሮቹ ዳግም ወደ ሊጉ አናት የሚመልሳቸው ድል ለማስመዝገብ ወደ ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።

በመጨረሻው መርሀ-ግብር መሪው መቻልን በማሸነፍ ወሳኝ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ በሁሉም መለክያዎች ጥሩ አቋም ላይ ይገኛል። ተከታታይ ድሎች ባስመዘገቡባቸው ስድስት መርሀ-ግብሮች ዘጠኝ ግቦች በማስቆጠር በአምስቱ መረባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡት ነብሮቹ በነገው ዕለት የድል ጉዟቸው ማስቀጠል ከቻሉ መሪነቱን ይቆናጠጣሉ።

ቡድኑ መቻልን በረታበት ጨዋታ ፈጣን የመስመር ሽግግርን በመተግበር በቶሎ ግብ አስቆጥሮ በሁለተኛው አጋማሽ አፈግፍጎ በመጫወት የሚፈልገውን አሳክቶ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን በነገው ጨዋታ ግን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግቡን ያላስደፈረው የፋሲል ከነማ የመከላከል አደረጃጀት በምን መልኩ አስከፍተው ጎል ያገኛሉ የሚለው ጉዳይ ከባድ ፈተና ይሆናል።

ከስምንተኛው ሳምንት በኋላ መነቃቃት እየታየበት ያለው ፋሲል ከነማ ከሁለት ድሎች በኃላ ከጣላቸው ሁለት ነጥቦች መልስ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ከሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና ይገናኛል።

ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ ጋር በጋራ በስድስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ፊት የተቀመጡት ዐፄዎች ከመጨረሻው ሳምንት የአቻ ውጤት ተላቀው ሦስት ነጥብ ማስመዝገብ ከቻሉ ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል የሚያገኙበት ዕድል የሰፋ ነው። በነገው ጨዋታ በድንቅ አቋም ላይ ከሚገኝ ቡድን ጋር መገናኘቱን ተከትሎ ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው እሙን ቢሆንም ላለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው የመከላከል አደረጃጀት ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ በሚያስችለው ጥሩ ብቃት ላይ መገኘቱ ጨዋታው ተጠባቂ ያደርገዋል።

ከውድድር ዓመቱ ጅማሮ ጥሩ የሚባል የተከላካይ ክፍል የገነቡት ዐፄዎቹ ሦስት ግቦች ካስተናገዱበት የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ሽንፈት ውጭ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ያስተናገዱበት ጨዋታ የለም። በነገው ጨዋታም የላቀ የአጨራረስ ብቃታቸውን እያሳዩ የሚገኙት ፈጣኖቹ የነብሮቹ አጥቂዎችን በምን አይነት አቀራረብ እንደሚያቆሙ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው።

በሀድያ ሆሳዕና በኩል እዮብ ዓለማየሁ፣ ዳግም ንጉሴ፣ በረከት ወንድሙ እና መለሰ ሚሻሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በፋሲል ከነማ በኩል ዮናታን ፍስሐ፣ ኪሩቤል ዳኜ እና በረከት ግዛው በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለስምንት ጊዜያት ተገናኝተው ሦስቱ ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀው ፋሲል ከነማ 4 ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ 1 ጊዜ አሸንፈዋል። በጨዋታዎቹም ዐፄዎቹ 11 ነብሮቹ ደግሞ 7 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።


ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ መድን

ለሳምንታት ሽንፈት ሳይቀምሱ የዘለቁት ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ መድን የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ መገባደጃ መርሀ-ግብር ነው።

በአስራ ስድስት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከአራት ጨዋታዎች በኃላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የጦና ንቦች ከውጤታማው የሦስት ሳምንታት የድል ጉዞ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። በተጠቀሱት መርሀ-ግብሮች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አራቱን ብቻ ማሳካታቸውን ተከትሎም በደረጃ ሰንጠረዡ አሽቆልቁለዋል። ዝቅተኛ ሽንፈት ካስተናገደው እና በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለት ነጥቦች ከሚበልጣቸው መድን ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ድል ማድረግም የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።

የጦና ንቦቹ ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ለሰባት የጨዋታ ሳምንታት ከሽንፈት መራቃቸው እንደ በጎ የሚነሳላቸው ነገር ቢሆንም በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው የጣሏቸው ነጥቦች ከመሪዎቹ ጎራ እንዲሸራተቱ ምክንያት ሆኗቸዋል። ውጤቶቹ ተከትሎ ከ3ኛ ደረጃነት ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለመውረድ የተገደደው ቡድኑ ከአቻ ውጤት ተላቆ ወደ ድል መንገድ መመለስ ይጠበቅበታል።

በፕሪምየር ሊጉ ጥቂት ሽንፈት እና ጥቂት ግቦች የተቆጠረበት ኢትዮጵያ መድን በአስራ ሰባት ነጥቦች 6ኛ ደረጃነት ተቀምጧል።

በመጨረሻው ሳምንት ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ያገኙት መድኖች አሁንም ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት ድል ማድረግ ይኖርባቸዋል።

መድኖች በሊጉ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ከማስተናገዳቸው በተጨማሪ ከጥሩ እንቅስቃሴ ጋር ነጥብ እየያዙ በመውጣት ላይ ይገኛሉ። ከሊጉ መሪ በሁለት ያነሰ የጨዋታ መጠን አድርጎ በስድስት ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ልዩነት አጥቦ ወደ ቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ለመሻገር በነገው ጨዋታ ታትሮ እንደሚጫወት ይታመናል።

ባለፍው የጨዋታ ሳምንት አራፊ የነበሩት ወላይታ ዲቻዎች በኢትዮጵያ ዋንጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው አብነት ደምሴ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ቅጣቱ ተሻግሮበት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ዓምና ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የራቀው መልካሙ ቦጋለ እና ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ይሆናል። ለሌሎች የቡድኑ አባላት የነገውን ጨዋታ የሚጠባበቁ ይሆናል። የመድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 2 ሲያሸነፍ መድን አንድ አሸንፎ በሦስት አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 8፣ መድን 5 ግቦች በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።