የመቻል ዋና አሰልጣኝ ለቀናት ቡድናቸውን አይመሩም

የመቻሉ ዋና አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ለቀናት ቡድኑን እንደማይመሩ ታውቋል።

ሊጉ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መልስ በአዳማ ከተማ መካሄድ ከጀመረበት ከ12ኛ ሳምንት አንስቶ እስከ ትናንት ቡድኑ ስሑል ሽረን እስከ ረታበት ጊዜ ድረስ የመቻል እግርኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድናቸውን እየመሩ እንዳልሆነ ታዝበናል።

ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት ህመም እንዳጋጠማቸው እና ህክምናቸውን በአግባቡ በመከታተል አሁን በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን ከህመመማቸው ለማገገም በቂ ዕረፍት እንዲያደርጉ በህክምና ባለሙያ የተገለፀላቸው በመሆኑ ከአስር ቀን በኋላ ቡድናቸው ከፋሲል ከነማ አልያም ከባህር ዳር ከተማ ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ወደ መደበኛ ስራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ማወቅ ችለናል።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ባሳለፍነው ዓመት መቻልን የተቀላቀሉ ሲሆን ዘንድሮ ለተጨማሪ ዓመታት ከቡድኑ ጋር አብሮ ለመቆየት ውላቸውን ማራዘማቸው ይታወቃል።