የማርቲን ኪዛ የ80ኛው ደቂቃ ግብ ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ እንዲጋሩ አስችላለች።
ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጨረሻው ጨዋታ መቻልን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው አራት ለውጦች ጫላ ተሺታ ፣ እዮብ ዓለማየሁ ፣ መለሰ ሚሻሞ እና ዳግም ንጉሴን አስወጥተው በምትካቸው ደስታ ዋሚሾ ፣ ሳሙኤል ዮሀንስ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ቃለዓብ ውብሸትን ሲጠቀሙ በአንፃሩ ከሀዋሳ ከተማ አቻ ተለያይተው የተመለሱት ፋሲል ከነማዎች በአንፃሩ ባደረጓቸው ለውጦች በረከት ግዛው ፣ ዮናታን ፍሰሃ ፣ ኪሩቤል ደሳለኝን አስወጥተው በምትካቸው ሀቢብ መሀመድ ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና አቤልን እንዳለን በመጀመሪያ ተመራጭነት አስጀምረዋል።
እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሀል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ነበር።
በሙከራ ረገድ ፍፁም ደካማ በነበረው አጋማሹ በ22ኛው ደቂቃ በሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል ብሩብ በየነ ከቀኝ መስመር የተሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ ምኞት ደበበን በግሩም ሁኔታ ካለፈ በኋላ ያደረጋት ሙከራ ዒላማዋን ሳትጠብቅ ቀረች እንጂ ሀዲያን ማድረግ የማድረግ የሚችል አጋጣሚ ነበር።
በ35ኛው ደቂቃ ግን ሀዲያ ሆሳዕናዎች በጨዋታው ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ እጅግ ድንቅ በነበረ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ከፋሲል ከነማ የማዕዘን ምት በተቋረጠ ኳስ የጀመረው የመልሶ ማጥቃት ብሩክ በየነ ከሰመረ ሃፍታይ የደረሰውን ቄንጠኛ ኳስ ተጠቅሞ በተረጋጋ አጨራረስ ሀዲያን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ አካላዊ ፍትግያዎች በበዙበት ቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ፋሲሎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በማርቲን ኪዞ አስገራሚ አክሮባቲክ ሙከራ አቻ ለመሆን ቀርበው የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ በመውጣቷ ጨዋታው በሀዲያ መሪነት ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ሁለተኛውን አጋማሽ ዣቪየር ሙሉ እና ቢኒያም ላንቃሞን ቀይረው በማስገባት የጀመሩት ፋሲሎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የሰነዘሩበት ነበር በተለይም በ51ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ዣቪየር ሙሉ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታት እና ያሬድ በቀለ በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በሂደት ተመጣጣኝ መልክን እየያዘ በመጣው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ረገድ አንፃራዊ የበላይነት መውሰድ ችለዋል ፤ በተለይም በ64ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዋሚሾ ከሳሙኤል ዮሀንስ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሯት የፋሲሉ የግብ ዘብ አማስ ኦባሶጊ በቀላሉ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበረች።
በብዙ መመዘኛዎች በሂደት እየተቀዛቀዘ በመጣው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች በ80ኛው ደቂቃ በማርቲን ኪዛ አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል ፤ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀው ዩጋንዳዊው አጥቂ የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ የሊግ ግቡን ያሬድ በቀለ መረብ ላይ አሳርፏል።
በማርቲን ኪዛ ግብ የተነቃቁ የሚመስሉት ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ደጋግመው የሀዲያን የግብ ክልል ቢጎበኙም ተጨማሪ ግብ ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተደምድሟል።