በሊቢያ ፕሪምየር ሊግ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው አማካይ ግብ አስቆጥሯል

ከነዓን ማርክነህ በአል መዲና መለያ ሁለተኛ የሊግ ግቡን አስቆጥሯል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት የሊቢያውን ክለብ አል መዲና የተቀላቀለው ኢትዮጵያዊ አማካይ ከነዓን ማርክነህ ቡድኑ አል ዋታንን ሦስት ለባዶ ባሸነፈበት የምሽቱ ጨዋታ በክለቡ መለያ ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሯል።

የትሪፖሊው ክለብ አል ኢትሀድ አል ሚስራቲን ሦስት ለባዶ ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ በመጀመርያ ጨዋታው የመጀመርያ ግቡን ማስቆጠር ችሎ የነበረው ተጫዋቹ ዛሬም ግብ በማስቆጠር የሊቢያ አጀማመሩን አሳምሯል።

በአራት ምድቦች ተከፍሎ በመካሄድ ላይ ባለው የሊቢያ ፕሪምየር ሊግ በምድብ አራት ላይ የሚገኙት አል መዲናዎች በአምስት ጨዋታዎች አስር ነጥቦች በመሰብሰብ ከከተማ ተቃናቃኛቸው አል አህሊ ትሪፖሊ በአምስት ነጥቦች ዝቅ ብለው በሁለተኛ ደረጃነት ይገኛሉ።