መረጃዎች| 54ኛ የጨዋታ ቀን

የ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል፤ መርሀ-ግብሮቹ የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ስሑል ሽረ

የጨዋታ ሳምንቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ስሑል ሽረ በሚያደርጉት ጨዋታ ይከፈታል

ወደ 6ኛ ደረጃነት ከፍ ያደረጋቸውን ድል በማስመዝገብ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ፈረሰኞቹ ሦስተኛ ተከታታይ ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል።


በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነገ ሦስተኛ ድላቸው የሚያስመዘግቡ ከሆነ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል የሚደላደሉበት ዕድል ያገኛሉ። ለተከታታይ ሳምንታት ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ወደ ውጤት ለመመንዘር ተዘግረው የቆዩት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ድል ባስመዘገቡባቸው ሁለት መርሀ-ግብሮች ላይ ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት መገንባታቸው ወደ ውጤት ጎዳና መልሷቸዋል። በተለይም በመቐለ 70 እንደርታ ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ ባከናወኗቸው ጨዋታዎች በብዙ ረገድ መሻሻል ያሳየው ቡድኑ የአፈፃፀም ክፍተቱ አርሟል። ቡድኑ ድል ባደረገባቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ከማስቆጠሩም በተጨማሪ የነበረው እንቅስቃሴ ቡድኑ መሻሻሉን ጠቋሚ ነው።

በነገው ጨዋታም በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሀ-ግብሮች አምስት ግቦች አስተናግዶ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድን እንደ መግጠማቸው በጨዋታው የተሻለ ግምት እንዲሰጣቸው ያደርጋል።

ከሳምንታት በኋላ መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ያገኙትን ድል ማስቀጠል ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች
በተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ወደ ወራጅ ቀጠናው ገብተዋል።

ስሑል ሽረዎጉልህ የሆነ የወጥነት ችግር የሚታይበት ቡድን ነው። ቡድኑ በተሸነፋባቸው ሁለት ጨዋታዎች ለክፉ የሚሰጥ እንቅስቃሴ ባያሳይም በሁለቱም አጋማሾች ወጥነት ያለው ብቃት ለማሳየት ሲቸገር ተስተውሏል። ከኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ከመቻል ባደረጓቸው ጨዋታዎች በሁለቱም አጋማሾች የነበራቸው የተለያየ ብቃትም ቡድኑ ከመርሀ-ግብሮቹ አንድም ነጥብ ሳያሳካ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል።

ከዚ በተጨማሪም በሊጉ የመጀመርያ ሳምንታት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የነበረው ቡድኑ በሂደት ጥንካሬውን አጥቷል፤ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አምስት ግቦች ከማስተናገዱም በላይ የነበረው ለጥቃት የተጋለጠ አደረጃጀት የኋላ ክፍሉ አሳስቶታል። አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በነገው ዕለት በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ውስን ተስፋ ያሳየው የማጥቃት አጨዋወት ማስቀጠል እንዲሁም ተጋላጭነቱ ጨምሮ ግቦች እያስተናገደ ያለው የኋላ ክፍላቸው የማሻሻል የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በቅጣት ምክንያት ከባለፈው ጨዋታ ውጭ የነበረው ፍፁም ጥላሁን ነገ ወደ ሜዳ ሲመለስ ከአዳማ ከተማ ጋር ነበረው ጨዋታ ጉዳት ያጋጠመው አጥቂው ቢንያም ፍቅሬ ለነገ ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። ባለፉት ጨዋታዎች ላይ በጉዳት ግልጋሎት ያልሰጠው ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉም ወደ ልምምድ የተመለሰ ቢመለስም ለነገጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠናል። የስሑል ሽረ የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በ2012 የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 2 ጊዜ ተገናኝተው ጊዮርጊስ አንዱን (4-0) ሲያሸንፍ አንዱን ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያይለዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ እና ከመጨረሻው ሳምንት ሽንፈት በቶሎ ለማገገም እያለሙ ወደ ሜዳ የሚገቡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአስራ ሦስት ነጥቦች 14ኛ ደራጃ ላይ የሚገኙት አዞዎቹ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ለመሸሽ በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ ድል ለማስመዝገብ አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።

አርባምንጭ ከተማዎች ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ሀዋሳ ከተማን አንድ ለባዶ በማሸነፍ መጠነኛ እፎይታ ማግኘት ቢችሉም በመጨረሻው የሊግ ጨዋታቸው በሲዳማ ቡና ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለት አሽቆልቁለዋል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች አስተናግዶ አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ የማጥቃት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማነቱ ቀንሷል። አዞዎቹ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታም ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በነገው ጨዋታ ወደ ድል መንገድ ዳግም ለመመለስም በአመዛዡ ቀጥተኛ አጨዋወት ላይ የተሞረኮዘው የማጥቃት አጨዋወታቸው ጥራት እና ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።


በአስራ አምስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚያስችላቸው ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል።

ወልዋሎን በመርታት የከተማውን ቆይታ በድል የጀመረው ቡድኑ በመጨረሻው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ ወደ ድል መመለስ ካልቻለ ይበልጥ ወደ አደጋው ክልል ይጠጋል፤ ይህንን ተከትሎም በተመሳሳይ ወደ ወራጅ ቀጠናው ላለመግባት ጠንክሮ ይጫወታል ተብሎ ከሚገመተው የቅርብ ተፎካካሪው ሦስት ነጥብ መውሰድ ግድ ይለዋል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዋች አንድ ድል፣ አንድ አቻ እና አንድ ሽንፈት የገጠመው ቡድኑ በጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ አራቱን ብቻ ማሳካት ቢችልም በእንቅስቃሴ ደረጃ ለክፉ የማይሰጥ ብቃት አሳይቷል፤ በተለይም ስድስት ግቦች ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት አጨዋወት የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ለረጅም ግዜ ከሜዳ ርቆ የቆየው ሳሙኤል አስፈሪ ከጉዳት ተመልሶ ልምምድ መስራት ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ አይደርስም። እንዲሁም አበበ ጥላሁንም ከጉዳት ቢመለስም የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።
በአዳማ ከተማ በኩልም ጉዳት ላይ ከነበሩት ዳግም ተፈራ እና ቢኒያም ዐይተን በተጨማሪ ሙሴ ካቤላም ለነገው ጨዋታ አይደርስም።

በሊጉ በ17 ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ስድስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 12 ግቦች ያስቆጠሩት አርባምንጮች ስድስት ጊዜ 10 ግብ ያስቆጠሩት አዳማዎች ደግሞ አራት ጊዜ ድል አድርገዋል።