በመጀመርያው አጋማሽ ፍፁም ጥላሁን ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወሳኝ ድል አሳክተዋል።
ፈረሰኞቹ በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠሩበት ጎል አዳማ ከተማን ከረቱበት ስብስባቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጦች ግብጠባቂውን ተመስገን ዮሐንስ፣ በረከት ወልዴ ፣ ቢንያም ፍቅሬን አስወጥተው በምትኩ ግብጠባቂው ባህሩ ነጋሽ፣ አማኑኤል ተርፉ እና ፍፁም ጥላሁን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በአንፃሩ በስሑል ሽረ በመቻል ከደረሰባቸው ሽንፈት ከስብስባቸው የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ክፍሎም ገ/ህይወት እና አሌክስ ኪቲካን አሳርፈው በመሐመድ አብዱልለጢፍ እና ዊልያም ሰለሞን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሔ ወልደፃድቅ በመሩት በዚህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ገና ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ በቁጥር በዝተው ወደ ፊት በመሄድ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር በኩል እጅግ የተሻሉ ነበር። በተለይ በ11ኛው ደቂቃ በተከላካዩ መሐመድ አብዱልለጢፍ እና በግብጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል መካከል በተደረገ ቅብብሎሽ ግብጠባቂው ፋሲል በተገቢው መንገድ ያላራቀውን ኳስ ተገኑ ነጋሽ ነፃ ኳስ አግኝቶ ወደ ጎል የመታውን ፋሲል በድጋሚ ያዳነበት ብዙም ሳይቆይ 13ኛው ደቂቃ ሄኖክ ዮሐንስ ኢላማን ሳይጠብቅ በመቅረቱ የመከነው ኳስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጭነው ለመጫወታቸው ማሳያ ነበር።
በጨዋታው ሽረዎች በ16ኛው ደቂቃ መሐመድ ከግራ መስመር ያሻገረውን አጥቂው ፋሲል አስማማው በግንባሩ በመግጨት ካደረገው ሙከራ በኋላ ፈረሰኞቹ በመልሶ ማጥቃት በሜዳ ቀኝ ክፍል ተገኑ ተሾመ ኳሱን ወደ ፊት በመግፋት ተጫዋች በመቀነስ ለአማኑኤል ኤርቦ ቢያቀብለውም ኳሱን ሊቆጣጠረው ባለመቻሉ ፍፁም ጥላሁን አግኝቶት በቀላሉ ወደ ጎልነት በመቀየር ለቡድኑ ቀዳሚውን ጎል አስቆጥሯል።
ጨዋታውን በተገቢው ሁኔታ ተቆጣጥረው ጫና በመፍጠር ደጋግመው ወደ ሳጥን የደረሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሚገባቸውን ጎል በ17ኛው ደቂቃ ካስቆጠሩ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ወደፊት በመሄድ ሙከራ ለማድረግ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ወስደውባቸዋል። በ35ኛው ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የግራ መስመር ተከላካዮ የሻይዱ የግል ብቃት ታክሎበት ወደ ውስጥ ያሻገረውን ተገኑ ኳሱን ተቆጣጥሮ ወደ ጎል የመታውን የግቡ ቋሚ የመለሰበትን ኳስ ዝግጁ ያልነበረው አማኑኤል ኤርቦ ኳሱን ወደ ላይ የላካት እና ያልተጠቀመበት አጋጣሚ ለፈረሰኞቹ ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል ጥሩ ዕድል ነበር።
በዚህ ሁሉ ሂደት በስሑል ሽረ በኩል ኳሱን ተደራጅተው በመያዝ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ለመውጣት እጅግ ሲቸገሩ በመጀመርያው አጋማሽ የጠራ የጎል ዕድል መፍጠር በኩል ተጠቃሽ ሙከራ አልታየም። በአንፃሩ ለዕረፍት መውጫ 43ኛው እና 45ኛው ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን እና ተገኑ ተሾመ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ቢሆንም ወደ ጎልነት ሳይቀይሩት የመጀመርያው አጋማሽ በፈረሰኞቹ የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት በሙከራ መታጀብ የጀመረው በ52ኛው ደቂቃ ጀምሮ ነበር። ከቀኝ መስመር አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ያሻገረውን ተቀይሮ የገባው አሌክስ ኪታታ በግንባሩ በመግጨት የሞከረው እና ከአምስት ደቂቃ በኋላ ከቅጣት ምት መሐመድ አብዱልለጢፍ በረጅሙ የላከውን ኳስ ሌላው ተቀይሮ የገባው ብሩክ ሀዱሹ በግንባሩ የመታውን ግብጠባቂው ባህሩ ነጋሽ በቀላሉ የያዘው ኳስ ሽረዎች በተሻለ የፈጠሩት የጎል ዕድል ነበር።
መጀመርያው አጋማሽ እንደነበራቸው ብልጫ ከአጋማሹ አንስቶ በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዘው የታዩት ፈረሰኞቹ በ66ኛው ደቂቃ አማኑኤል ኤርቦን መነሻ ያደረገውን ኳስ ፍፁም ተቀብሎ ወደ ውስጥ የላከውን ተገኑ ተሾመ እጅግ ያለቀለት የግብ ዕድል ኢላማውን ሳይጠብቅ ያመከነው ኳስ አስቆጪ ሆኖ አልፏል።
ሽረዎች እንደወሰዱት ከፍተኛ ብልጫ ጎል ፍለጋ ወደ ፊት በመሄድ ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የጎል አጋጣሚ በመፍጠር በኩል ሲቸገሩ ተስተውሏል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የጥንቃቄ አጨዋወት በመምረጥ በቁጥር በራሳቸው ሜዳ በዝተው አልፎ አልፎ ወደ ፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል። ሻይዱ ከማዕዘን ምት አሻግሮት ተገኑ በግንባሩ የመታውን ግብጠባቂው ፋሲል ኳሱን ተቆጣጥሮ ወደ ፊት ለአጥቂዎች የላከውን የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ ሄኖክ ዮሐንስ አግኝቶ የግብጠባቂው ፋሲልን መውጣት ተመልክቶ ከርቀት የመታው ለጥቂት ወጥቶበታል።
ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የተነቃቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ የሽረን የግብ ክልል ሲፈትሹ ታይተዋል። በ85ኛው ደቂቃ አፈወርቅ ኃይሉ አምቻችቶ የሰጠውን ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን የተገናኘው አማኑኤል ኤርቦ ሳይጠቀምበት ግብጠባቂው ፋሲል ያዳነበት እና የግብጠባቂ ባህሩ ነጋሽ ጉዳትን ተከትሎ በተሰጠው ዘጠኝ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ተገኑ ተሾመ እጅግ ክፍት የጎል አጋጣሚ በአሰጋኸኝ ጴጥሮስ ሲያመክን እንዲሁም 96ኛው ደቂቃ ለማመን የሚከበድ ግብጠባቂውን አማኑኤል ኤርቦ አልፎ ተቀይሮ ለገባው መሐመድ ኮኔ ሰጥቶት ኮኔ የመታውን የግቡ ቋሚ ሲመልሰው ሌላው ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ ጉልላት አግኝቶ የሱሑል ሽረው ተከላካይ አሰጋኸኝ በድጋሚ ጎል እንዳይሆን አድርጎት ጨዋታው በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።