ሪፖርት | አዞዎቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

አዞዎቹ በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠሩት ሁለት ግቦች አዳማ ከተማን 2-0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል።

አርባምንጭ ከተማ በ12ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱበት ቋሚያቸው አንዱዓለም አስናቀ እና ፍቃዱ መኮንን አሳርፈው አህመድ ሁሴንን እና ብሪያን አህቡዋን ይዘው ሲቀርቡ አዳማ ከተማ በ13ኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረቱበት ቋሚያቸው ሙሴ ከበላ ፣አድናን ረሽድ እና አሜ መሃመድን አሳርፈው ዳንኤል ድምሴ ፣ ሙሴ ኪሮስን እና አሸናፊ ኤልያስን ይዘው ቀርበዋል።


ሁለቱ ከሽንፈት ማግስት የተገናኙ ቡድኖችን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ቀዝቀዝ ባለ አጀማመር ጀምሮ እምብዛም ሙከራዎች ሳይታይበት እስከ አስረኛው ደቂቃ ድረስ ዘልቋል። ሁለቱም ቡድኖች የተሳካ የኳስ ቅብብል እንኳን ማድረግ ባይችሉም አዞዎቹ በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል ደርሰው በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ ጨዋታው እየቆመ ለመጀመር ተገዷል። አዳማ ከተማም በአንፃሩ መረጋጋት ተስኗቸው የተሳካ የኳስ ንክኪ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውለዋል።

እንዲህ እያለ ጨዋታ ቀጥሎ አዞዎቹም ቀዳሚ መሆን የቻሉበት ኳስ በ13ኛው ደቂቃ ላይ መረብ ላይ አክለዋል። ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ብሪያን አህቡዋ አግኝቶ በመጀመሪያ ንክኪ መሬት ለመሬት ያሻገረለትን ኳስ አህመድ ሁሴን ፍጥነት ተጠቅሞ በመድረስ በቀላሉ ወድግብነት ቀይሮታል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታው መመለስን ምርጫቸው ያደረጉት አዳማ ከተማዎች ኳስ ከግብ ጠባቂያቸው ጀምረው መስርተው ሲጫወቱ የተስተዋሉ ሲሆን ዘለግ ላለ ደቂቃ የኳስ ንክኪ ብልጫ ወስደው የአቻነት ግብ ፍለጋ የአዞዎቹ ተከላካይ መስመር ላይ ጨናዎችን አጠንክረው እስከ ሰላሳዎቹ ደቂቃ መጨረሻ ድረስ ቀጥለዋል።

ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብ ቀይረው ነጥብ ማስቀጠል ላይ ትኩረት ያደረጉት አዞዎቹ በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ፈጥነው የአዳማን አንደኛውን የሜዳ ክፍል መርገጥ ቢችሉም ይዘው ሚገቡትን በረከት ያሉ ኳሶችን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው 40ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ መሪነታቸውን ማስፋት የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በመልስ ውርወራ የተገኘውን ኳስ ቡታቃ ሸመና  ከመሃል ሜዳ አከባቢ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ ጥሎለት በግራ መስመር በኩል ሲጠባብቅ የነበረው በፍቅር ግዛው ኳሱን በፍጥነት ደርሶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በብልሃት ኳሱን በግብ ጠባቂው እግር ስር በማሳለፍ  ከመረብ ጋር እንዲትገናኝ አድርጎ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ እንዲል አስችሏል። አጋማሹም በአዞዎቹ ሁለት ለምንም ተጠናቋ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታ ጥሩ ጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክቷል። አዳማ ከተማ ለግብ ፍለጋ እጅግ ጠንከር ብለው ጫናዎችን በማሳደር ላይ አተኩረው በአንድ ለአንድ ቅብብል ቀጥለውም በረጃጅም ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት ሲገሰግሱ ቢስተዋሉም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸዋል። አዞዎቹ በአንፃሩ የግብ ጥማታቸው በሁለት ብቻ አልበቃ ብሎ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ በፈጣን ሽግግር ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። በ74ኛው ደቂቃ ላይ ጠንከር ያለ ሙከራ አድርገዋል። በአንድ ለአንድ ቅብብል በቻርለስ ሪባኑ የተሻገረውን ኳስ ብራያን አምኩዋ ከሳጥን ውጭ ሆኖ አክርሮ  የመታውን ኳስ የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ የመለሰበት አጋጣሚ ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ ጠንከር ያለ ሙከራ ነበር።

ሁለቱም ቡድኖች ወደፊት እየሄዱ ነገር ግን አስቆጪ የሚባል አጋጣሚዎችን ሳይፈጥሩ ጨዋታው ወደመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃ ሲያመራ የአዳማ ከተማ ጫና እየበረታ የግብ ፍላጎታቸው ጥረት ጨምሮ አጋጣሚዎቹን ወደግብ ለመቀየር ሲጠሩ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ጠንካራ ሆኖ ያመሸውን ከናፈቀው ድል ጋር ለመገናኘት በሚገባ ተልዕኮውን እየተጠወጣ የዘለቀው የአዞዎቹ ተከላካይ መስመር እንደጠበቁት ሊሆንላቸው ባለመቻሉ ወደ ግብ ቀርበው ከባድ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ይልቁንስ አዞዎቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ የግብ ማግባት ሙከራ አከታትለው ሲያደርጉ ለመመልከት ችለናል።


በዚህም ሁለት ከሸንፈት መልስ የተገናኙ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ብቻ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት በአዞዎቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።፡