ዐፄዎቹ ናይጄሪያዊ ግብ ጠባቂያቸውን ሸጡ

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ፋሲል ከነማን ተቀላቅሎ የነበረው ናይጄሪያዊው አማስ ኦባሶጊ ከአራት ወራት የዐፄዎቹ ቤት ቆይታ በኋላ ወደ ሌላ የአፍሪካ ክለብ አምርቷል።

ባለፈው የክረምት የዝውውር መስኮት ዐፄዎቹን ተቀላቅሎ ቡድኑን በማገልገል ላይ የቆየው ናይጀርያዊ ግብ ጠባቂ አማስ ኦባሶጊ በ50 ሺህ ዶላር የዝውውር ሂሳብ ወደ ታንዛንያው ሲንጊዳ ብላክስታርስ ማምራቱን የተጫዋቹ ወኪል ቢኒያም ሚደቅሳ አረጋግጦልናል።

የናይጄሪያ ፕሪምየር ሊግ የወርቅ ጓንት ሽልማትን ካሸነፈበት የቤንደል ኢንሹራንስ ቆይታው በኋላ ላለፈትን ወራት በኢትዮጵያዊው ክለብ ቆይታ የነበረው ይህ ግብ ጠባቂ በዐፄዎቹ ቤት ውሉን ለተጨማሪ አንድ ዓመት የማራዘም አማራጭ ያለው የሁለት ዓመት ኮንትራት ቢፈራረምም ከወራት ቆይታ በኋላ ከክለቡ ተለያይቶ ትናንት ወደ ታንዛንያ አምርቷል።

በክለቡ በኩል ስለሁኔታው ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አመራሮቹ ስልክ ባለማንሳታቸው ምክንያት የእነርሱን ምላሽ ሳናካትት የቀረን ሲሆን በተያያዘ መረጃም ዐፄዎቹ በአማስ ኦባሶጊ ምትክ ሌላ የውጭ ግብጠባቂ ለማምጣት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አውቀናል።