መረጃዎች| 57ኛ የጨዋታ ቀን

የ14ኛ ሳምንት በነገው ዕለት ይገባደዳል፤ የጨዋታ ሳምንቱ መቋጫ የሆኑ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በተመሳሳይ ነጥብ በደረጃ ሰንጠርዡ ተከታትለው የተቀመጡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ መነቃቃት አሳይተው የነበሩት ዐፄዎቹ በሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው በመውጣት ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል አባክነዋል።

የአሰልጣኝ ውበተ አባተው ፋሲል ከነማ የመከላከል ጥንካሬውን ማስቀጠሉ ዋነኛው ጠንካራ ጎኑ ነው፤ ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ ጥንካሬውን ማስመስከር ችሏል።

በመጨረሻው ሳምንት ጠንካራውን ሀድያ ሆሳዕና የገጠመው ቡድኑ የተሻለ እንቅስቃሴ ባደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ ግብ አስቆጥሮ ነጥብ ቢጋራም የፊት መስመር ውጤታማነቱ ወደ በፈለገው ደረጃ ይገኛል ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው። በነገው ጨዋታም ባለፉት አራት መርሀ-ግብሮች መረቡን ካላስደፈረው ኢትዮጵያ ቡና እንደመገናኘቱ የፊት መስመሩን ጥንካሬ አንድ ደረጃ ከፍ አድርጎ መቅረብ ይጠበቅበታል።

በውድድር ዓመቱ አራት ድል፣ አራት ሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤት በማስመዝገብ አስራ ስድስት ነጥቦች የሰበሰቡት ቡናማዎቹ ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።

እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የገነቡት ቡናማዎቹ በመጨረሻዎቹ አራት መርሀ-ግብሮች መረባቸውን አላስደፈሩም።
ቡድኑ ከሽንፈት አልባው የአራት ሳምንታት ጉዞ በፊት በተከናወኑ ስድስት ጨዋታዎች አራት ሽንፈቶች አስተናግዶ አስከፊ የውጤት ማጣት ካደረገ ወዲህ በተከታታይ ጨዋታዎች ከሽንፈት መራቁ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ጉልህ የወጥነት ችግር ይስተዋልበታል። በውድድር ዓመቱ በተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑ በነገው ዕለት ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ለውጦች ማድረግ ይኖርበታል። የባለፈው ዓመት ጠንካራው የመከላከል ጥንካሬያቸው መልሰው ያገኙት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በተለይም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመራቸው ማሻሻል ቀዳሚ የቤት ስራቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በፋሲል ከነማ በኩል ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት መሰለፍ ያልቻሉት ዮናታን ፍስሐ ፣ ኪሩቤል ዳኜ እና በረከት ግዛው የነገውም ጨዋታ እንደሚያመልጣቸው ሲታወቅ በተጨማሪም ቢኒያም ላንቃሞ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ታውቋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ መላኩ አየለ አሁንም ከጉዳት ባለማገገሙ ከነገው ጨዋታ ውጪ ነው።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ እስካሁን አስራ አምስት ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን ፋሲል ከነማ አምስት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሦስት ድሎችን ሲያሳኩ ቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማዎች በእነዚህ ጨዋታዎች አስራ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ አስራ ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)

ኢትዮጵያ መድን ከ ሀዋሳ ከተማ

ከላይ እና ከታች ባለው ፉክክር ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያገናኘው እና ለሁለቱም ተጋጣሚዎች ወሳኝ የሆነው ጨዋታ 9:00 ላይ ይካሄዳል።

ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ወደ መሪዎቹ ጎራ የተቀላቀሉት ኢትዮጵያ መድኖች በነገው ዕለት ማሸነፍ ከቻሉ 2ኛ ደረጃነትን ይረከባሉ።

11 ጨዋታዎችን አከናውነው 13 ጨዋታዎች ካከናወነው መሪው መቻል በአምስት ነጥቦች ተበልጠው በ5ኛ ደረጃ የሚገኙት መድኖች ከሁለቱም ቀሪ ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ መሰብሰብ ከቻሉ የሊጉን መሪነት የመረከብ ዕድል ይኖራቸዋል። ይህንን ተከትሎም ከጨዋታው የሚያገኙት ሙሉ ነጥብ ወሳኝነቱ ትልቅ እንደ መሆኑ በልዩ ትኩረት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በውድድር ዓመቱ አንድ ሽንፈት ብቻ በመቅመስ ብቸኛ ክለብ የሆነው መድን ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ አምስት ግቦች አስቆጥሮ ሁለት ጨዋታዎችን በመደዳ በማሸነፍ ወደ ነገው ፍልምያ ይቀርባል። ቡድኑ በነገው ዕለትም በተለመደው አኳኋን ኳስ በመያዝ እንዲሁም የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቹን ፍጥነት ያማካለ የማጥቃት አጨዋወት ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በመጨረሻው ጨዋታ በውስን መልኩ ካለወትሮ ለመልሶ ማጥቃቶች ሲጋለጥ የነበረው የመከላከል አደረጃጀቱ ክፍተት መቅረፍ ግን ቀዳሚ ስራው መሆን ይኖርበታል። ቡድኑ ጋቶች ፓኖምን ማጣቱን ተከትሎ ካለ ተፈጥሮአዊ የአማካይ ተከላካይ በጀመረበት ጨዋታ ትልቅ ፈተና ባይገጥመውም ከሌላው ጊዜ አንፃር የነበረው ተጋላጭነት ግን ከፍ ያለ ነበር።

በነገው ዕለትም ተጋጣሚው የፈጣን የመልሶ ማጥቃት ቁልፍ መሳርያዎች የሆኑ እንደነ ዐሊ ሱሌይማን የመሳሰሉ ተጫዋቾች የያዘ ቡድን እንደ መሆኑ የመጨረሻውን መርሀ-ግብር ክፍተቶቹን አርሞ መቅረብ ግድ ይለዋል።

አስር ነጥቦች ሰብስበው ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት ሀይቆቹ ከሳምንታት በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ ጠንካራውን መድን ይገጥማል።

ድል ካደረጉ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት ሀይቆቹ በውድድር ዓመቱ ሁለት ድል፣ ስድስት ሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ በወራጅ ቀጠናው ላይ ይገኛሉ።
ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች ከድል ጋር ከመራራቁም በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የግብ ማስቆጠር ችግር ውስጥ ገብቷል። ኳስና መረብ ካገናኘ አራት ጨዋታዎች ማስቆጠሩም የችግሩ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም ብያንስ አንድ የደረጃ መሻሻል ለማግኘት እና ከአደጋው በመጠኑ ፈቀቅ ለማለት ሙሉ ውጤት ያስፈልገዋል። ይህ እንዲሆን ግን በውድድር ዓመቱ አራት ግቦችን ብቻ ላስተናገደው ጠንካራውን የመድን የኋላ ክፍል የሚመጥን የማጥቃት አጨዋወት ማበጀት ግድ ይላቸዋል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል አጥቂው አብዲሳ ጀማል በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ስለመሆናቸው ሰምተናል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ ዮሴፍ ታረቀኝ ከቡድኑ ጋር አሁንም አይገኝም። ተከላካዩ ወንድማገኝ ማዕረግ ደግሞ ባስተናገደው የልምምድ ጉዳት መሰለፉ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ 29 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 13 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው የመጨረሻ ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ጨምሮ በ12 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተው መድን 4 ጨዋታ አሸንፏል። ሀዋሳ ከተማ 38 ፣ መድን 28 አስቆጥረዋል።