ኢትዮጵያ መድኖች በሰንጠረዡ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ያሉበትን ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።
ኢትዮጵያ መድኖች ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ዋንጫ ቱት በበረከት ካሌብ ተክተው ሲገቡ ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው በባህርዳር ከተማ ሽንፈት ከገጠመው ቋሚ ሰይድ ሀብታሙ፣ ሲሳይ ጋቾ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ፣ ዳዊት ታደሰ እና አቤኔዘር ዮሐንስን በምንተስኖት ጊንቦ፣ በረከት ሳሙኤል፣ እንየው ካሳሁን፣ አማኑኤል ጎበና እና ታፈሰ ሰለሞን ተክተው ገብተዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር ከማራኪ እንቅስቃሴ ጋር ያስመለከተን የመጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ ነበር። በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ነበር። ቢንያም በላይ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ አብርዶ ለአማኑኤል ጎበና አቀብሎት አማካዩ ለዐሊ ሱሌይማን አመቻችቶለት አጥቂው ከግቡ አፋፍ ሆኖ መቷት አቡበከር ኑራ እጅግ በሚያስደንቅ ብቃት ባዳናት ሙከራ የጀመረው ጨዋታው ግብ ያስተናገደው በ13ኛ ደቂቃ ላይ ነበር። ሀይደር ሸረፋ ከራሱ የግብ ክልል በረዥሙ አሻግሯት መሐመድ አበራ ከግብ ጠባቂው በላይ አሳልፎ ከመረቡ ጋር የቀላቀላት ኳስም መድንን መሪ ያደረገች ግብ ነበረች።
ወደ ሙከራነት ያልተቀየሩ በርካታ የግብ ዕድሎች በታየበት አጋማሽ መድኖች ሀይደር ሸረፋ እና ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጭ አክርረው በሞከሯቸው ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ስያደርጉ ሀይቆቹ በተባረክ ሄፋሞ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ተጫዋቹ በነፃ በነፃ አቋቋም ሆኖ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ያገኛት ኳስ መቶ አቡበከር ኑራ ያዳናት ኳስም ለግብ የቀረበች ነበረች።
እንጀ መጀመርያው አጋማሽ ጠንካራ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎች የመድኖች ብልጫ ቢታይበትም የኋላ ኋላ ግን ሀዋሳ ከተማዎችም ጥሩ በመንቀሳቀስ ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል።
በመድኖች በኩል ረመዳን የሱፍ ከሳጥኑ የግራ ክፍል አሻግሯት አለን ካይዋ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳናት ሙከራ ትጠቀሳለች። በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ ቢንያም በላይ፤ ዓሊ ሱሌይማን ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ መቷት አቡበከር ኑራ የመለሳት ኳስ እንዲሁም ዓሊ ሱሌይማን ከተከላካይ መስመር በረዥሙ የተሻገረችውን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ መቷት አቡበከር ኑራ ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራ ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው።
በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቅያ ደቂቃ ግን በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ዳዊት ተፈራ የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ በአግባቡ ያላራቃትን ኳስ አግኝቶ ከመሀል ሜዳው አካፋይ ግሩም የረዥም ርቀት ግብ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጎ ጨዋታው ተጠናቋል።
ጨዋታው በመድን የሁለት ለባዶ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ በ23 ነጥቦች በ2ኛ ደረጃነት ተቀምጧል።