መረጃዎች| 58ኛ የጨዋታ ቀን

በርከት ያሉ ተጠባቂ ጨዋታዎች የሚከናወኑበት የ15ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ ነገ ይጀመራል፤ መርሀ-ግብሮቹን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ብርቱካናማዎቹ እና ፈረሰኞቹ የሚያደርጉት ጨዋታ በሳምንቱ ተጠባባቂ ከሆኑ መርሀ-ግብሮች አንዱ ነው።

ሊጉ ከመቀመጫ ከተማቸው ወደ አዳማ ከተማ ከተዘዋወረ በኋላ ድል ማድረግ ያልቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በሁለት ነጥብ የሚበልጣቸውን ቡድን ላይ ድል መጎናፀፍ የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።
ብርቱካናማዎቹ ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዘው መውጣር ካልቻሉ በደረጃ ሰንጠርዡ ወገብ ባለው የነጥብ መቀራረብ ምክንያት ምናልባትም የደረጃ መንሸራተት ሊገጥማቸው ስለሚችል የነገው ጨዋታ ወሳኝ ነው።

ብርቱካናማዎቹ ከሊጉ አስደናቂ አጀማመራቸው ማግስት ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ። በመጨረሻ ካደረጓቸው አራት የሊግ ጨዋታዎች በተከታታይ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አራቱን ብቻ ያሳካኩት ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ድል መንገድ በመመለስ በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ ለመውጣት የነገውን ጨዋታ ይፈልጉታል።
በመጀመርያ ሳምንታት በነበረው የፈጠራ እና የግብ ማስቆጠር ብቃት ላይ የማይገኘው ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን አንድ ነው። በነገው ዕለት የሚኖረው የአፈፃፀም ጥራትም በቡድኑ ውጤት ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።

በሀያ አንድ ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ መሪዎቹን ይበልጥ ለመጠጋት ከዚህ ተጠባቂ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ይኖርባቸዋል።

በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ የቻሉት ፈረሰኞቹ ሰሞነኛ ጥሩ ብቃታቸው ከመሪዎቹ ጎራ እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተከታታይ ድሎቹ በፊት በተከናወኑ አመዛኙን ጨዋታዎቻቸውን በጥሩ ብቃት ቢከውኑም ከጥሩ እንቅስቃሴ በዘለለ ድል ማስመዝገብ ባለመቻላቸው ወደ ፉክክሩ እንዳይጠጉ አድርጓቸዋው ቆይቷል።
በቅርብ ሳምንታት ግን ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ደረጃቸው ለማሻሻል በቅተዋል። አሁንም በሰንጠረዡ የላይኛው ክፋ ዘላቂ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ ድሎችን ማስመዝገብ ያስፈልጋቸዋል።


ፈረሰኞቹ በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ አጋጣሚዎ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ከወጡባቸው እና ጠንካራ የመከላከል ቁጥሮች ካስመዘገቡባቸው መርሀ-ግብሮች በኋላ ግቦችን ማስተናገድ ጀምረዋል። በነገው ጨዋታም ከተጋጣሚያቸው አሁናዊ የፊት መስመር ጥንካሬ አንፃር ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም የመከላከል መዋቅራቸው የቀደመ ጥንካሬ የመመለስ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ24 ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14ቱን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 5ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል። ፈረሰኞቹ 38፣ ብርቱካናማዎቹ 20 ጎሎች አስቆጥረዋል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ጥረት አልተሳካም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አማኑኤል ኤርቦ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን በረከት ወልዴ ደግሞ ከቅጣት መልስ ነገ ቡድኑን የሚያገለግል ይሆናል። ባለፈ ጨዋታ በጉዳት ያልነበረው አጥቂው ቢንያም ፍቅሬ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ሲሰማ በአንፃሩ ተከላካይ አማኑኤል ተርፉ ለነገ ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጭ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው ፍልሚያ ዝግጁ መሆናቸውን ሰምተናል።

ስሑል ሽረ ከ አርባምንጭ ከተማ

ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ወደ ሜዳ የሚገቡት ስሑል ሽረዎች በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ የሚያልሙት አዞዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው ስሑል ሽረ ቀስ በቀሰ እየተዳከመ ወራጅ ቀጠናው ላይ ገብቷል፤ ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በሊጉ መቐለን ከማሸነፉ ውጭ በመልካም ጎኑ የሚነሳለት ነገር ያለ አይመስልም።

ኳስ ይዞ በፈጣን ሽግግር ለመጫወት ሀሳቡ ያለው የሚመስለው ስሑል ሽረ በቅርብ ሳምንታት የመከላከል ጥንካሬውን መልሶ ማግኘት ሲቸገር እና በርከት ያሉ ግቦች ሲቆጠርበት ይታያል። ይህ ደግሞ እንደነገ ተጋጣሚው ጉልበታም እና ፈጣን አጥቂዎች ካሉት ቡድን ጋር ሲገናኝ አደጋ ላይ ሊጥለው የሚችል ደካማ ጎኑ ነው። ቡድኑ አምስት ግቦች አስተናግዶ ከተሸነፈባቸው ሁለት መርሀ-ግብሮች በኋላ ባከናወነው የመጨረሻው የሊግ ጨዋታው ሽንፈት ብያስተናግድም የሚቆጠሩበትን ግቦችን መቀነሱ እንደ በጎ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም የመከላከል አደረጃጀቱ አሁንም መሻሻል የሚገባው ድክመት ነው። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመርም ችግርም ሌላው መቀረፍ የሚገባው የቡድኑ ድክመት ነው።

አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ሁሉንም የቡድኑ ድክመቶች በአንዴ ለማስተካከል የሚቸግራቸው ቢሆንም የመከላከል አደረጃጀቱ ችግር መቅረፍ ውጤት ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ግን መናገር ይቻላል።

በእስካሁኑ ጨዋታዎቹ አምስት ድል እና ስድስት ሽንፈት የገጠመው አርባምንጭ ከተማ በአስራ ስድስት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በውድድር ዓመቱ ከወልዋሎ ጋር በጣምራ ዝቅተኛ የአቻ ውጤት (1) ያስመዘገበው ቡድኑ በውጤት ረገድ ሞቅ ቀዝቀዝ የሚለው አካሄዱ ለነገው ጨዋታ የሚመጣበትን አኳኋን አጠራጣሪ ያደርገዋል።

በእርግጥ ቡድኑ በመቻል እና ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት አስተናግዶ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ መበርታቱ እና አምስት ግቦች ካስተናገደባቸው ሁለቱ ጨዋታዎች መልስ በአራት የጨዋታው ሳምንታት አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ በጥንካሬውን ዘልቆ የነበረው የመከላከል ጥንካሬው መልሶ ማግኘቱ በአወንታነቱ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ለማድረግ የወጥነት ችግር የሚታይበት የማጥቃት ክፍሉ ማሻሻል ይኖርበታል።

የፊት መስመር ተጫዋቾቹን ጨምሮ ከኳስ ውጭ በታታሪ ተጫዋቾች የተገነባው የአዞዎቹ ቡድን በነገው ዕለትም ቀጥተኛ እና መልሶ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። በነገው ጨዋታም በዋነኝነት የቡድኑ የማጥቃት መሰረት የሆነው ታታሪው አሕመድ ሑሴን እና በፍቅር ግዛው ከስሑል ሽረ ተከላካዮች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ እጅግ ተጠባቂ ይሆናል።

በስሑል ሽረ በኩል ፋሲል አስማማው እና ዋልታ ዓንደይ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ እና አበበ ጥላሁን ከቡድኑ ጋር ቀለል ያለ ልምምድ መስራት ቢችሉም ለጨዋታው ብቁ እንዳልሆኑ ሲታወቅ አሸናፊ ተገኝ ጉዳቱ ለረጅም ግዜ ከሜዳ ይርቃል። እንዲሁም የእንዳልካቸው መስፍን የነገው ጨዋታ ላይ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።