ሪፖርት | ፈረሰኞቹ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን ተቀዳጅተዋል

የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ባህሩ ነጋሽ የግብ ተሳትፎ ባደረገበት ጨዋታ ፈረሰኞቹ ብርቱካናማዎቹን ረተዋል።

ድሬዳዋ ከተማ በ14ኛው ሳምንት ከመቻል ጋር አቻ ከተለያየው የመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸው አቤል አሰበ እና ተመስገን ደረሰን አሳርፈው በምትካቸው ሱራፌል ጌታቸው እና ሙኸዲን ሙሳን ይዘው ሲገቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ በ14ኛው ሳምንት ስሑልል ሽረን ከረቱበት ቋሚ ስብስባቸው አማኑኤል ተርፉ እና አማኑኤል ኤረቦ አስቀምጠው በረከት ወልዴን እና ቢንያም ፍቅሩን ይዘው ቀርበዋል።


ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የ15ኛ ሳምንት ቀዳሚው ጨዋታ ቡድኖች የኳስ ብልጫ ለመውሰድ በአጫጭር ቅብብል ተረጋግተው ቢጫወቱም በሙከራ ረገድ ደካማ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራ ሳይደረግበት በቀጠለው በአጋማሹ ፈረሰኞቹ ወደፊት ገፍተው ጫና ያሳደሩበት ሲሆን ብርቱካናማዎቹም በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀርቶ ይዘው ሚሄዱትን ኳስ በቀላሉ እየተቀሙ የግብ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ተመልክተናል።

ጨዋታው 32ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከመልስ ውርወራ የተጀመረውን ኳስ ቢንያም ፍቅሩ ወደ ግብ አሻግሮት የብርቱካናማዎቹ ተከላካዮች የሰሩት ስህተት በመጠቀም የፈረሰኞቹ በረከት ወልዴ ከፍፁም ቅጣት መምቻ ሳጥን ውጪ ላይ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ አላዛር ማረን የመለሰበት አጋጣሚ የአጋማሹ ብቸኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ፈረሰኞቹ ጠንከር ብለው ተመልሰው ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 50ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂ ባህሩ ነጋሽ በረጅሙ ኳስን ወደ ግብ አሻምቶ የብርቱካናማዎቹ ተከላካይ ኢስማኤል አብዱጋኒዩ ኳሷን በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ኳሷ ተጨርፋ ከመረብ ጋር ተገናኝታለች።

ጫናዎችን አጠንክሮ የቀጠሉት ፈረሰኞቹ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ብዙም አልቆዩም። በ53 ደቂቃ ላይ ከመሃል ሜዳ የተሰነጠቀለትን ኳስ ተገኑ ተሾመ በፍጥነት ደርሶ ይዞ ሲገባ የብርቱካናማዎቹ ግብ ጠባቂ አላዛር ማረነ ጥፋት ፈፅሟል በሚል ፍፁም ቅጣት ምት ለፈረሰኞቹ ሲሰጥ ግብ ጠባቂው በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ፍፁም ቅጣት ምቱንም ፍፁም ጥላሁን ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ብርቱካናማዎቹ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ጫናዎችን ተቋቋመው በእርጋታ ኳሶችን ይዘው ወደፊት በመሄድ የግብ ሙከራ አጋጣሚ ሲፈጥሩ ቢስተዋሉም አደገኛ የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ ደቂቃዎች ገፍተዋል። በ70ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው መስዑድ መሐመድ ከሳጥን ትንሽ ርቆ የቆመ ኳስ ወደ ግብ መጥቶ ለትንሽ ከፍ ያለበት አጋጣሚ ይታወሳል።

ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር በርከት ብለው ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲደርሱ ተመልክተናል።

ጨዋታው ወደመገባደጃ ሲቃረብ ብርቱካናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው የፈረሰኞቹን ተከላካዮች የፈተኑ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ፈረሰኞቹ በተቃራኒው ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደፊት ከመሄድ ተቆጥበው ወደ መከላከሉ በማድላት የብርቱካናማዎቹን ጫና ለመቋቋም ሲጥሩ አስተውለናል ፤ በዚህም ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት በፈረሰኞቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።